ክፍለ ጊዜ 11/21
ገጽ 2/4 ማንነትን ለመገንባት በርካታ መነሻዎች ያሉት ሰው መሆንማንነትን ለመገንባት በርካታ መነሻዎች ያሉት ሰው መሆን
እንዲህ ያሉት የልጅነት ተሞክሮዎች ህጻናት ስለ ማንነታቸው እና ትክክለኛ ቦታቸው የት እንደሆነ ግልጽ የሆነ ሀሳብ እንዳይኖራቸው የባሰ ያከብድባቸዋል። ህጻናት ራሳቸውን የሚያዩት ከወላጆቻቸው ጋር አንድ አድርገው በመሆኑ እገዛ ካላገኙ ስለ ራሳቸው የሚኖራቸው ሀሳብ አብዛኛውን ጊዜ አሉታዊ ወይም የተምታታ ይሆናል። ችግሮቹ ምንድን ናቸው፤ እንዲሁም የአደራ ቤተሰብ እንክብካከቤ ላይ እያሉ ስለራሳቸው አዎንታዊ የሆነ አስተሳሰብን እንዲያዳብሩ ህጻናትን የምትረዱትስ እንዴት ነው?
ህጻኑ የአደራ ቤተሰብ እንክብካቤ እንዲያገኝ ሲመደብ አብዛኛውን ጊዜ የሚከተለውን ዓይነት የታማኝነት ግጭት ያጋጥመዋል፡- “ከወላጄ(ወላጆቼ) ጋር ተቆራኝቼአለሁ፤ ነገር ግን አሁን ደግሞ የአደራ ቤተሰብ ወላጆቼ ትኩረት እና ፍቅር እየሰጡኝ ነው። የጥፋተኝነት ስሜት ወይም ወላጆቼን እንደከዳሁ ሳይሰማኝ ይህን ልቀበል የምችለው እንዴት ነው?”
የተፈጥሮ ወላጆቹ የአደራ ቤተሰቡ ላይ ያልተፈቱ ችገሮች (ንዴት፣ ቅናት) ካሏቸው እና የልጃቸውን ልብ እንደሰረቁባቸው ሰዎች አድርገው የሚያዩአቸው ከሆነ ይህ በህጻኑ ውስጥ የሚፈጠር ግጭት ይበልጥ ስቃይ ሊፈጥርበት ይችላል። ልጃችሁን ሌላ ሰው እንዲንከባከበው መወሰን ከባድ ነው፤ “አዲሱ ቤተሰብ” የበለጠ ሀብት ያለው ሲሆን ደግሞ የባሰ ይከብዳል።
በሌሎች ክፍለ ጊዜዎች ውስጥ እንደተገለጸው በጣም ትንሽ ዕድሜ ላይ ያሉ ህጻናት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከአደራ ቤተሰብ ወላጆቻቸው ጋር ጥልቅ ቅርርቦችን የመመስረት ሁኔታ አላቸው። ይህ የተፈጠረ እንደሆነ ህጻኑ “እማማ” ወይም “አባባ” ብሎ ሊጠራችሁ የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ። ይህን ልትቀበሉት ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ህጻኑ ዕድሜው እየጨመረ ሲመጣ የራሱን የጀርባ ታሪክ መገንዘብ የሚችልበት የግድ መንገድ ማግኘት እንዳለበት ማወቅ አለባችሁ። ምን አልባት ህጻኑ ወይም ድክ ድክ የሚለው ልጅ እንደ ወላጁ ያያችሁ ይሆናል። ነገር ግን የተፈጥሮ ቤተሰቦችም እንዳሉት ከትንሽ ዕድሜ ጀምሮ ሊያውቅ እና ሊገነዘበው ይገባል። ሦስት ወይም አራት ዓመት አካባቢ ሲሞላው አብዛኛውን ጊዜ “ሁለት እናቶች እና አባቶች አሉህ” ብላችሁ ማውራት መጀመር ትችላላችሁ። ይህ መደረግ ያለበት “ትክክለኛ ወላጆቹ” እንዳልሆናችሁ ህጻኑ ከሌሎች ህጻናት ወይም አዋቂዎች ከመስማቱ በፊት ነው።
ህጻኑ ታማኝነቱን ለሁለት እንዲያካፍል የሚገደድበት ከባድ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ሲባል የአደራ ቤተሰብ ወላጆች ስለ ልጁ ወላጆች የሚሰሟቸው እነዚህ ተፈጥሮአዊ የሆኑ ስሜቶች መፈታት አለባቸው (ይህ ደግሞ ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው)። የተፈጥሮ ወላጆቹ ላይ የሚኖር ማንኛውንም ንዴት ወይም ጥላቻ ህጻኑ የሚያየው የራሱ ማንነት አንድ አካል ላይ እንዳነጣጠረ ንዴት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አንድ የአደራ ቤተሰብ ልጅ በራሱ ፈቃድ የተፈጥሮ ወላጆቹን ሊወቅስ ወይም ሊረሳቸው ሊሞክር ይችላል፤ ነገር ግን ይህ የሚያስከትለው ውጤት ህጻኑ አንድ ወገኑ ከተፈጥሮ ወላጆቹ ጋር እንዲሁም ሌላኛው ወገኑ ደግሞ ከአደራ ቤተሰብ ወላጆቹ ጋር ተጣብቆ ሀሳቡ ሁለት ቦታ እንዲከፈል እና እነዚህን አንድ ላይ አዋህዶ ስለ እራሱ ግልጽ የሆነ አንድ ሀሳብ እንዳይኖረው ማድረግ ነው። ይህ ዞሮ ዞሮ በተለይም ደግሞ የአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ታዳጊው እንደ አዋቂ ማንነቱን ለመገንባት በሚሞክርበት ወቅት በህጻኑ ላይ ችግር መፍጠሩ አይቀርም። ህጻኑ አዲስ የስነ-ልቦና ዕድገት ደረጃ ላይ በደረሰ እና ስለ እራሱ ይበልጥ የበሰለ ግንዛቤ ባገኘ ቁጥር ስለ ማንነቱ እና ስለ ጀርባ ታሪኩ አዲስ ሀሳብ መገንባት ይኖርበታል፤ ስለዚህ ይህ ብዙ ዓመታት የሚወስድ ሂደት ነው።
በተጨማሪም ስለ ወላጆቹ ያሏችሁ አመለካከቶች ራሱን ማክበር እና ስለማንነቱ ኩራት ሊሰማው ስለመቻሉ ለህጻኑ የሚያስተላፉት መልዕክት አለ (ስለ ወላጆቹ አሉታዊ አመለካከቶችን መያዝ ህጻኑ ለራሱ አሉታዊ ግምት እንዲሰጥ ያደርጋል)። ህጻኑን ለማገዝ ሲባል ስለ የተፈጥሮ ወላጆቹ ከልብ አዎንታዊ የሆነ አመለካከትን ማዳበር እንደ የአደራ ቤተሰብ ወላጅ በጣም ከባድ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው።
አስተያየት የሚሰጥባቸው እና ውይይት የሚደረግባቸው ጥያቄዎች