ክፍለ ጊዜ 14/21

ገጽ 1/7 የስልጠና ክፍለ ጊዜ፡- በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆችን ከልጅነት እስከ አዋቂነት ማሳደግ እና አመራር መስጠት

የስልጠና ክፍለ ጊዜ፡- በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆችን ከልጅነት እስከ አዋቂነት ማሳደግ እና አመራር መስጠት

ልምምድ የሚደረግባቸው ችሎታዎች፡- 

  • ጉርምስና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ባሉ ልጆች እንዲሁም በቤተሰብ ላይ የሚያስከትላቸውን የተለመዱ ተግዳሮቶች መገንዘብ
  • ቁጥጥርን በአግባቡ ማድረግ እና የነጻነት አስፈላጊነት፡- ከመቆጣጠር ይልቅ ስምምነት ማድረግ
  • ስለ ጉርምስና ከህጻናት እና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ካሉ ልጆች ጋር ግልጽ ውይይቶችን ማቀድ እና ማድረግ
  • የራሳችሁን የህይወት ልምድ እንደ ግብዓት መጠቀም

የክፍለ ጊዜው ጭብጥ፡-
በዚህ የስልጠና ክፍለ ጊዜ ከልጅነት ወደ አዋቂነት በሚያደርጉት ሽግግር ውስጥ (ማለትም አንድ ህጻን ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ እንዲሁም በኋላ ላይ ወደ አዋቂነት በሚገባበት እና ራሱን ችሎ የራሱን ህይወት መኖር በሚጀምርበት ሂደት ውስጥ) ህጻናትን እንዴት መደገፍ እና መምራት እንደምትችሉ ትወያያላችሁ እንዲሁም ታቅዳላችሁ።  

የክፍለ ጊዜው ዓላማዎች፡- 
የክፍለ ጊዜው ዓላማ አንድ ህጻን ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ በሚገባበት ወቅት በቤተሰቡ ውስጥ የሚኖሩትን ለውጦች እንዲሁም እንክብካቤ ሰጪዎች ከልጅነት ወደ አዋቂነት የሚደረገውን ሽግግር መደገፍ የሚችሉበትን መንገድ መገንዘብ እና ማስተዳደር ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች ነጻነትን በሚፈልጉበት ወቅት እንክብካቤ ሰጪዎች አብዛኛውን ጊዜ ትእዛዝ ከማክበር ጋር በተያያዘ ችግር ይገጥማቸዋል። በተጨማሪም ብዙ አሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ አፍሪካውያን በፍጥነት በመለወጥ ላይ ባለው ዓለማችን ውስጥ የሚከተለው አስቸጋሪ ግጭት ያጋጥማቸዋል፡- እኔ ማን ነኝ፤ በዚህ ህይወት ውስጥ ማድረግ ያለብኝስ ምንድን ነው? የሚል ማለት ነው፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆችን ለማገዝ ሲባል የዚህ ክፍለ ጊዜ ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

  • በውይይት አማካኝነት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆችን ለጉርምስና ማዘጋጀት
  • ቁጥጥርን እና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለውን ልጅ ስምምነት ማድረግ ውስጥ ማሳተፍን አመጣጥኖ ማስኬድ
  • ህጻኑ ከልጅነት ወደ አዋቂነት እንዲሸጋገር ለመደገፍ የሚያስችል ጠንካራ ግንኙነት መመስረት