ክፍለ ጊዜ 11/21

ገጽ 3/4 ብዙ የጀርባ ታሪኮቻቸውን እንዲገነዘቡ ህጻናትን ማገዝ - የሚመከሩ መልመጃዎች

ብዙ የጀርባ ታሪኮቻቸውን እንዲገነዘቡ ህጻናትን ማገዝ – የሚመከሩ መልመጃዎች

ሀ. እንክብካቤ መስጠት መፈለግ እና መቻል ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው
ሞያ በተላበሰ መልኩ ለህጻኑ ወላጆች አክብሮት ማሳየት የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ህጻኑን በሚከተለው መልኩ ማናገር ሊሆን ይችላል፡-

ወላጆችህ ሁል ጊዜም በጥሩ መልኩ ሊንከባከቡህ ይፈልጉ እንደነበረ እርግጠኛ ነኝ። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ምንም ያህል ቢፈልጉም እንኳን ለልጆቻቸው መስጠት የሚፈልጉትን ያህል ፍቅር መስጠት የሚችሉት ሁሉም ወላጆች አይደሉም። ምንም እንኳን የሚወዱህ ቢሆንም ወላጆችህ በህይወታቸው ውስጥ ብዙ ችግሮች እንዳሉባቸው ታውቃለህ (እንደሚከተለው ያሉ ህጻኑ ሊረዳቸው የሚችሉ ምሳሌዎችን መስጠት ትችላላችሁ፡– “እናትህ መጠጣት የጀመረችው እሷ ራሷ ገና ህጻን ልጅ እያለች ነበር፤ ስለዚህ አሁን ምንም ያህል ብትሞክር በአጭሩ መጠጣት ማቆም አትችልም ”)
በጣም ኃለፊነት የተሞላበት ነገር ያደረጉት እና በጣም የሚከብድ ነገር ለማድረግ የወሰኑትም ለዚህ ነው፡- አንተን በጥሩ ሁኔታ እንዲንከባከቡህ ሌሎች ሰዎችን ለመጠየቅ የወሰኑት ማለት ነው! ምን አልባት በቀጥታ አልጠየቁም ይሆናል፤ ነገር ግን ችግሮቻቸውን ገልጸው ሲያሳዩ አንተን ለማዳን እርዳታ መጠየቃቸው ነበር (በቀጥታ ይህን ማለት ከብዷቸው ነው እንጂ)።
ስለዚህ ወላጀችህ ለአንተ የሚቻላቸውን ለማድረግ ይሞክራሉ። በእኛ ሲናደዱ ወይም ሲቀኑ እና አንተን መልሰው ማግኘት ሲፈልጉም እንኳን አንተን ስለሚወዱህ እና ሌሎች ሰዎች አንተን እንዲንከባከቡህ መፍቀድ ስለሚከብዳቸው እንደሆነ እናውቃለን። በውስጣቸው ይህ ለእነሱ በጣም ከባድ እንደሆነ ያውቁታል፤ ነገር ግን እንክብካቤ ሊሰጡህ እንደሚፈልጉ ያሳዩሀል። ይህን ሲያደርጉ እኛ በእነሱ አንናደድባቸውም፤ አንተን እንድንንከባከብህ እኛን መጠየቃቸው ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን እንዲቀበሉ ልናግዛቸው እንሞክራለን እንጂ።

ለ. “ሁለት እናቶች እና ሁለት አባቶች አሉህ – ታድለህ!”
ያለበትን ሁኔታ እንዲገነዘብ ህጻኑን ለማገዝ ሲባል የሚከተለው ማብራሪያ በአደራ ቤተሰብ እና በተፈጥሮ ወላጆች መካከል ከሚኖር ግጭት ነጻ የሆነ አመለካከትን የሚያንጸባርቅ ነው፡-

“ዕድለኛ እንደሆንክ ታውቃለህ አይደል – ጥሩ ህይወት ሊሰጡህ የሚፈልጉ ሁለት እናቶች አሉህ፤ እንዲሁም ጥሩ ህይወት ሊሰጡህ የሚፈልጉ ሁለት አባቶች አሉህ። ወላጆችህ በጣም ጥሩ ነገር ነው ያደረጉት፡- አንተን ወልደውሀል፤ ለዘጠኝ ወራትም የእናትህ ሆድ ውስጥ ነበርክ። ወላጆችህ ሲደክማቸው እንክብካቤ እንድንሰጥህ ወደ እኛ መጣህ። ስለዚህ ሊንከበከቡህ የተስማሙ አራት ወላጆች አሉህ ማለት ይቻላል። አንዳችን ማድረግ የማንችለውን ሌሎቻችን ማድረግ እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ ባንስማማም ሁላችንም በተቻለን መጠን ምርጥ በሆነ መልኩ ልንንከባከብህ ስለምንፈልግ ብቻ ነው።

ሐ. “የተለያዩ መነሻዎች እንቆቅልሹን” አንድ የማንነት ሀሳብ አድርጎ መገንባት
ለዚህ እንቅስቃሴ መቀሶች፣ ፕላስተር፣ የተወሰኑ ትላልቅ ወረቀቶች እና የተለያዩ ቀለሞች ያሏቸው እርሳሶች ወይም ከለሮች ያስፈልጓችኋል። ለህጻኑ ይበልጥ የሚስማሙት ከሆነ እንደ ዳቦ ወይም የዛፍ ቅጠሎች ወይም ጠቃሚ ሆነው የምታገኟቸውን ሌሎች ማቴሪያሎችን መጠቀም ትችላላችሁ። እያንዳንዱ ዕቃ ህጻኑ የሚቀርበውን ወይም ይቀርበው የነበረን አንድ ሰው የሚወክል ይሆናል።

እንቅስቃሴው ከአምስት እስክ አሥራ አምስት ዓመት ካላቸው ህጻናት ጋር ሊከናወን ይችላል። አንድ ወይም ሁለት ከሠዓት በኋላ ሊወስድ ይችላል እንዲሁም ህጻኑ ዕድሜው ተለቅ ሲል እና ስላለበት ሁኔታ ይበልጥ ግንዛቤ ሲኖረው ሊደገም ይችላል።

በመጀመሪያ ህጻን “እስከዛሬ ድረስ ተንከባክበውህ የሚያውቁ ሰዎችን በሙሉ” ወረቀቱ ላይ በተለያዩ ምድቦች ሳል ብላችሁ ትጠይቁታላችሁ (ወይም እንዲስል ታግዙታላችሁ)። እያንዳንዱ ምድብ የራሱ ቀለም፣ ስም ወይም ሌላ ዓይነት ጠቋሚ ሊኖረው ይገባል።

አያቶች፣ እህቶች እና ወንድሞች፣ አስቀድሞ ተመድቦባቸው የነበሩ እንክብካቤ ሰጪዎች፣ ሲወለድ ያዋለዱት አዋላጅ እና ሀኪም፣ የአደራ ቤተሰብ ወላጆቹ እና ልጆቻቸው፣ ህጻኑ የሚቀርበው ውሻ ወይም የቤት እንስሳ፣ ጎረቤት፣ በቤተሰቡ ውስጥ ያሉ ሌሎች የአደራ ቤተሰብ ልጆች፣ የትምህርት ቤቱ ልጆች፣ ወዘተ ሊኖሩ ይችላሉ። ጊዜ ወስዳችሁ ህጻኑ መፍጠር የሚችላቸውን ያህል ብዛት ያላቸው ምድቦች እንዲፈጥር አግዙት።

እያንዳንዱ ምድብ ከሚከተሉት ጥያቄዎች ውስጥ የተወሰኑትን መርጣችሁ ህጻኑን ጠይቁት። ህጻኑን መልስ የሚሆን አንድ ቃል እንዲያገኝ ጠይቁት። ህጻኑ ምንም ቢመልስ የሚመለከተው ምድብ ላይ አንድ ቃል ወይም ምልክን አኑሩ።

 

  • “ስለዚህ ሰው (ወይም ስለነዚህ ሰዎች) የምታስታውሰው በጣም ጥሩ ነገር ምንድን ነው?” (ቃሉን/ምልክቱን ጻፉ)
  • “የዚህ ሰው በጣም ጥሩ ነገሩ ምንድን ነው” (የሚያምር ጸጉር/ድምጽ፣ ፍቅር፣ ርህራሄ፣ ጥንካሬ፣ ወዘተ)
  • “ይህ ሰው ለአንተ ያደረገው በጣም ምርጥ ነገር ምንድን ነው” (አንተን መውለድ፣ ልደትህን ማስታወስ፣ ወዘተ)
  • “ስለዚህ ሰው የሚያስቅህ ነገር ምንድን ነው –እሱን በጣም አስቂኝ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?” (ለምሳሌ፡- አረማመዱ፣ የሚላቸው በጣም ወጣ ያሉ ነገሮች፣ አንዳንድ የተለዩ ልማዶቹ፣ ወዘተ)
  • “ከዚህ ሰው ያገኘኸው ምርጥ ነገር ምንድን ነው” (ድፍረት፣ ጥንካሬ፣ ጽናት፣ መልካም ጤና፣ ሉጫ ጸጉር፣ ወዘተ)
“እኔ ማን ነኝ?” የሚለውን እንቆቅልሽ መፍታት

በመቀጠል አዲስ ወረቀት ትወስዱ እና ህጻኑን የራሱን ቅርጽ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ወረቀቱን በሚሞላ መልኩ በትልቁ እንዲስል ጠይቁት (ወይም አግዙት)። ህጻኑን ከራሱ ቅርጽ ስዕል በላይ ስሙን ወይም ምልክት እንዲያስቀምጥ ጠይቁት እና እንዲህ በሉ፡-

“አሁን አንተ ማን እንደሆንክ ልናውቅ ነው! እኛ ማለት በመንገዳችን ላይ ሌሎች ሰዎች ሲሰጡን ከቆዩአቸው ነገሮች የተሰራን ነን። ሰዎች የሚሰጡንን ጥሩ ነገሮች እያነሳን እንደምንጭን የጭነት መኪኖች ነን። ማን እንደሆንክ ማወቅ ማለት ሌሎች ሰዎች የሰጡህ ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ ማለት ነው፤ እና በጣም ብዙ ጥሩ ስጦታዎች የሰጡህ ይመስለኛል! በህይወትህ ውስጥ ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝተሀል ስለዚህ አሁን የምናደርገው ነገር ከባድ እንቆቅልሽ እንደመፍታት ነው!”

እንደ ዳቦ፣ ድንጋይ፣ ቅጠሎች ያሉ ዕቃዎችን እና ሌሎች ነገሮችን የምትጠቀሙ ከሆነ መሀሉ ላይ አንድ ዕቃ አስቀምጣችሁ እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ፡- “ይህ አንተ እና የጭነት መኪናችሁ ናችሁ። አሁን ሰዎች የሰጡህን ጥሩ ነገሮች እናግኝ እና ጭነት መኪናው ላይ እንጫናቸው። ከዚያ ምን ያህል ጥሩ እና ጠንካራ ሰው እንደሆንክ ማየት እንችላለን!” ይህ ዕቃ በጣም ሩህሩህ የነበረችው አያትህ ናት፤ ጭነት መኪናው ላይ እንጫናት እና አንተም ሩህሩህ ትሆናለህ! ይሄ ደግሞ ይወድህ የነበረው ውሻህ ነው፤ ፍቅር እንዲሰማህ ውሻውን ጭነት መኪናህ ላይ እንጫነው። እንደዚያ እንደዚያ እያለ ይቀጥላል። ህጻኑ ለጠቀሳቸው ሰዎች በሙሉ ይህንን አድርጉ።

ወረቀት እና እርሳስ የምትጠቀሙ ከሆነ፡-

አሁን ደግሞ ምድቦቹ እና ጠንካራ ጎኖቻቸው ያሉበትን የመጀመሪያውን ወረቀት ውሰዱ እና ለእያንዳንዱ ምድብ የተሰጡትን ቃላት/ምልክቶች ጨምሮ እያንዳንዱን ምድብ ቆርጦ እንዲያወጣ እና ተቆርጦ የወጣውን እያንዳንዱን ወረቀት በራሱ ሰውነት ቅርጽ የሰራው ስዕል ላይ እንዲለጥፍ ህጻኑን ጠይቁት። ህጻኑ ምድቦቹን ወይም ሰዎቹን የራሱ ሰውነት ቅርጽ ስዕል ላይ ማስቀመጥ ያለበት ትክክለኛ ቦታቸው ላይ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ይወደው ከነበረ ተቆርጦ የወጣው ወረቀት መቀመጥ ያለበት ከህጻኑ ልብ አጠገብ ነው። አንድ ሰው ጥሩ አዳማጭ ከነበረ ተቆርጦ የወጣውን ወረቀት ጆሮዎቹ ላይ አስቀምጡ፣ ወዘተ።

መ. ማንነትን በመገንባት ሂደቱ ላይ መወያየት – ትግሉ
 
በዕድሜ ተለቅ ላሉ ልጆች (ዕድሜያቸው 10 ዓመት አካባቢ እና ከዚያ በላይ ለሆኑ) እና ለወጣቶች ይህን ቪዲዮ መመልከት አብራችሁ ልታደርጉት የምትችሉት ነገር ሊሆን ይችላል። ከዚያም በዚህ ፊልም ውስጥ ዩስታ ስለምትናገረው ነገር እና በህይወቷ ውስጥ ከነበሩት የተለያዩ እንክብካቤ ሰጪዎች ጋር በተያያዘ የነበሯትን ተሞክሮዎች መሰረት በማድረግ ራሱን የቻለ ማንነት ስለገነባችበት መንገድ ውይይቶችን ልታደርጉ ትችላላችሁ። በዚህ ሂደት ውስጥ ዩስታ ባቀረበቻቸው ጉዳዮች ላይ ስላሉት/ሏት አስተያየቶች ከታዳጊው/ዋ ጋር ልትወያዩ ትችላላችሁ፡- ስለነበሯት የተለያዩ እንክብካቤ ሰጪዎች፣ ስለመለያየቶች፣ ተመሳሳይ ተሞክሮዎች እንክብካቤ በምታደርጉለት ህጻን ላይ ስላሳደሩት ተጽዕኖ፣ ህጻኑ ይህን ነገር ለመቋቋም እና ስለ እራሱ እና ስለ ሌሎች ሰዎች የራሱን አመለካከት ለመያዝ ስለሚሞክርበት መንገድ።
ሠ) የአደራ ቤተሰብ ልጃችሁን ስለማንነቱ የራሱን ታሪክ እንዲፈጥር ማገዝ

ይህን ቪዲዮ አብራችሁ ካያችሁት እና ከተወያያችሁበት በኋላ ፍቅር፣ ጥንካሬ ስለሰጡት፣ ስላሳቁት ሰዎች፣ ወዘተ በሙሉ ታሪክ እንዲናገር ወይም እንዲጽፍ ህጻኑን ወይም ወጣቱን ልታበረታቱት ትችላላችሁ።

ካሜራ ካላችሁ ተመሳሳይ ቪዲዮ መስራት ትቸላላችሁ። ይህ ህጻኑ በጣም ይቀርባቸው ስለነበሩ ሰዎች ሊሆን ይችላል። ህጻኑ የተለያዩ የኋላ ማንነቶች (የመነሻ ምንጮች) ያሉት በመሆኑ ምን እንደሚሰማው ሊገልጽ ይችላል።
ይህም ሁለት ቤተሰቦች ያሉት ሰው መሆንን የመቀበል ሂደትን ያካትታል። እንደዚህ ገና በልጅነት ዕድሜ ይህን ሁሉ ተሞክሮ ማሳለፍ ስላሉት አዎንታዊ እና ደስ የሚሉ ገጽታዎች አውሩ።

የእነዚህ እንቅቃሴዎች ዓላማ

እነዚህ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ዓላማቸው ተመሳሳይ ነው፡-የህጻኑን የኋላ ማንነት (መነሻ) እንደምትቀበሉ እና ስለእነዚህ ነገሮች እና የተለያዩ የኋላ የማንነት ምንጮች ያሉት ሰው ከመሆን ጋር ስለተያያዙ ችግሮች ለመወያየት ፈቃደኛ መሆናችሁን ለህጻኑ በተግባር ማሳየት ነው።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያገኛቸው የተለያዩ ሰዎች በሙሉ አዎንታዊ ነገር እንደሰጡት እና እነዚህ አዎንታዊ ነገሮች ዛሬ ያለው ማንነት አካል መሆናቸውን ማሳየት ነው።

በተጨማሪም ስለ ራሱ አዎንታዊ አስተሳሰብን እንዲያዳብር ህጻኑን የምታግዙት መሆኑን ያካትታል።

ይህ ሂደት ህጻኑ በእንክብካቤ በሚያሳልፋቸው ዓመታት ውስጥ ካለማቋረጥ ይቀጥላል።