ክፍለ ጊዜ10/15

ገጽ 1/7 በተጨባጭ ሥራዎች ግንኙነቶችን ማጠናከር

ተጨባጭ ሥራዎችን በመጠቀም ግንኙነቶችን ማጠናከር ይሠራል

የክፍለ ጊዜው ጭብጥ፡-

በክፍለ ጊዜ 6 (የእንክብካቤ ሞያን መለማመድ የሚቻልበት መንገድ) ውስጥ ተጨባጭ የሆኑ የዕለት ተዕለት ተግባራትን በማከናወን ላይ እያላችሁ እንዴት ግንኙነቶችን ማጠናከርን መለማመድ እንደምትችሉ ተምራችኋል። በተጨማሪም ህጻናቱን እንዴት በዕለት ተዕለት ተግባራት ውስጥ ማሳተፍ እና ያንን በምታደርጉበት ጊዜ ከእነሱ ጋር መስተጋብር መፍጠር እንደምትችሉ ተምራችኋል። በዚህ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ደግሞ መስተጋብሮችን መቆጣጠር ስለሚቻልበት መንገድ እና ህጻኑን ስለ ገደቦች እና ኃላፊነቶች ማስተማር ስለሚቻልበት መንገድ ትማራላችሁ።

አብዛኛውን ጊዜ በእንክብካቤ ላይ ያሉ ህጻናት እና ወጣቶች የእኔ የሚሉት ቦታ እንደሌላቸው ሊሰማቸው ይችላል። ከአካል እና ከስሜት አንጻር መታለፍ የሌለባቸውን መስመሮች ላያውቁ እና በአደራ ቤተሰቡ የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ስላሉት ኃላፊነቶች እና የማይታለፉ መስመሮች ግንዛቤ ላይኖራቸው ይችለል።

በእንክብካቤ ላይ ያሉ በርካታ ህጻናት በግንኙነት ውስጥ ማሳየት ስላለባቸው ባህሪ እና  በቤተሰብ ውስጥ ያለውን የዕለት ተዕለት አካሄድ እንዴት መከተል እንዳለባቸው ያልተማሩ ናቸው። የማይታለፉ መስመሮችን በማወቅ ረገድ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። የት እና መቼ ስለምን ማውራት እና ያለማውራት አለባቸው? የማይታለፉ አካላዊ እና ማህበራዊ መስመሮችን ማክበርን እንዴት መማር ይችላሉ?

ለምሳሌ አንድ ህጻን የሌላን ህጻን ነገሮች ሳይጠይቅ መውሰድ ይችላል? አንድ ህጻን ምግብ በማዘጋጀት ማገዝ ወይም የቤት ሥራውን መሥራት እንዳለበት ያውቃል? እርስ በእርስ የምናወራው ጮክ ብለን ነው ወይስ ድምጻችንን ዝቅ አድርገን ነው?

ይህ ህጻኑ እንዲሁም የአደራ ቤተሰቡ ሌሎች አባላት በሂደት የሚማሩት ነገር ነው።

በአደራ ቤተሰቡ የግንኙነት መረብ ውስጥ ህጻኑ የተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ በጣም የተለያዩ ባህሪዎችን ሊያሳይ ይችላል (ለምሳሌ፡- ቤት ውስጥ ብዙ ግጭቶች ውስጥ መግባት፤ ት/ቤት ደግሞ ምንም ግጭት ውስጥ ያለመግባት፤ ወይም በተገላቢጦሽ)። በዚህም የተነሳ የህጻኑ ጉዳይ በሚመለከታቸው ሰዎች መረብ ውስጥ የተለያዩ ሰዎች  (የአደራ ቤተሰብ ወላጆች፣ መምህር፣ አስጠኚ) ህጻኑን የሚያዩበት መንገድ በጣም የተለያየ ሊሆን ይችላል። ህጻኑ ህይወቱን ምን ያህል በአግባቡ እየመራ ነው እና በምን መልኩ መያዝ አለበት የሚሉትን ጉዳዮች በተመለከተ ብዙ ያለመግባባት ሊኖር ይችላል። የህጻኑን ወይም የታዳጊውን ፍላጎቶች በተመለከተ በግንኙነት መረቡ ውስጥ ባሉ ሰዎች መካከል መግባባትን ለማጠናከር የአደራ ቤተሰብ ወላጆች በምን መልኩ መሥራት ይችላሉ?

የክፍለ ጊዜው ዓላማዎች፡-

በዕለት ተዕለት መስተጋብሮቹ ውስጥ የህጻኑን ማህበራዊ ዕድገት መደገፍ። አንድ አዲስ ህጻን ወደ ቤተሰቡ በሚገባበት ወቅት አዲስ ኃላፊነቶችን እንዲያገኝ እና ገደቦች የሚቀመጡባቸው መንገዶችን እንዲያበጅ የአደራ ቤተሰቡን በማነሳሳት ሁሉም የቤተሰቡ አባላት መረጃው እንዳላቸው እና ተገቢው ክብር እንደተሰጣቸው እንዲሰማቸው ማድረግ። ህጻኑ በሚኖርበት አካባቢ ባለው የግንኙነት መረብ ውስጥ ባሉ ሰዎች መካከል ህጻኑን እና የሚያስፈልጉትን ነገሮች በተመለከተ የጋራ መግባባትን መፍጠር።

  ልምምድ የሚደረግባቸው ችሎታዎች፡-

  • በአደራ ቤተሰቡ ውስጥ ግንኙነቶችን እንዲገነባ ለህጻኑ አስተማማኝ መሠረት ሆኖ እንዲያገለግለው የግል እና የአካላዊ ነጻነት ስሜቱን ማጠናከር።
  • እንክብካቤ እንዲያገኙ የተመደቡትን ህጻናት የቤተሰቡ አካል እንደሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ እና በቤተሰቡ የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ምን አይነት ባህሪ ሊኖራቸው እንዲገባ እንዲማሩ ማገዝ።
  • የአደራ ቤተሰቡ አባል እንደመሆናቸው መጠን ሁሉንም የቤተሰብ አባላት ኃላፊነታቸውን እና ማለፍ የሌሉባቸውን መስመሮች በማወቅ ሂደት ውስጥ ማሳተፍ።
  • ሁሉም ሰው የህጻኑ ፍላጎቶች ምን እንደሆኑ እና ህጻኑ በትክክል መኖር እንዲችል ማገዝ ስለሚቻልበት መንገድ የጋራ ስምምነት ላይ እንዲደርስ የአደራ ቤተሰቡ የግንኙነት መረብ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ተቀናጅቶ መስራት።

   

  አንዲት እንክብካቤ ሰጪ ውይይት በማድረግ በተጨባጭ ሥራዎች ወቅት ከግንኙነት ጋር የተያያዘ ሥራ መሥራት ትችላለች። ለምሳሌ እንክብካቤ ሰጪዋ ስለራሷ የልጅነት ጊዜ ልታወራ ወይም ስለ ህጻኑ ደህንነት ጥያቄዎችን ልትጠይቅ ትችላለች።