ክፍለ ጊዜ 16/21
ገጽ 2/6 መግቢያ፡- ጨዋታ ምንድን ነው?መግቢያ፡- ጨዋታ ምንድን ነው?
በሁሉም ባህል ውስጥ ህጻናት እና አዋቂዎች ይጫወታሉ። ነገር ግን ጨዋታ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ለምንድን ነው? ጨዋታ የህጻናት የማሰስ ባህሪ አንድ አካል ነው፡- አንድ ህጻን የመተማመን ስሜት የሚሰማው ከሆነ ማሰስ፣ መጫወት እንዲሁም ከእንክብካቤ ሰጪዎች እና ከሌሎች ህጻናት ጋር ማህበራዊ መስተጋብር ማድረግ ይጀምራል። አንድ ህጻን ጨዋታ በሚጫወትበት ወቅት አንጎሉ ማደግ ይጀምራል እንዲሁም በኋላ ላይ በህይወት ውስጥ የሚያስፈልጉትን የሚከተሉትን ወሳኝ መሰረታዊ ክህሎቶች ይለማመዳል፡- ሚዛኑን መጠበቅ፣ የሰውነቱን ክፍሎች መቆጣጠር እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት የሚያስፈልጉ ደንቦችን መማር። አንድ ህጻን ፍጹም የሆነ ክህሎት እስከሚያዳብር ድረስ አንድን ጨዋተ መልሶ መላልሶ ሲጫወት ልታዩት ትችላላችሁ። ጨዋታ የመጀመሪያው ትምህርት መማሪያ መንገድ ነው።
ጨዋታ ህጻናት ትምህርት ላይ ያላቸውን ብቃት ያሻሽላል እንዲሁም ለአዋቂነት ህይወት የሚያስፈልጓቸውን የሚከተሉትን ክህሎቶች በማስተማር ያዘጋጃቸዋል፡- ትኩረት፣ የማስታወስ ችሎታ፣ አንድን ክህሎት ለማግኘት ስኬታማ ያልሆኑ ብዙ ሙከራዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የመቀበል ችሎታ፣ በጋራ በምንጫወትበት፣ በምንደንስበት ወይም በምንዘምርበት ወቅት ከሌሎች ሰዎች ጋር የመቻቻል እና የመናበብ ችሎታ፣ ወዘተ።
ጨዋታን በተመለከተ በጣም ዋናው ነገር የሚከተለው ነው፡- አዝናኝ መሆኑ! ከባድ ጭንቀት ያሉባቸው እና ያዘኑ ህጻናትም እንኳን በጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ ስትጋብዟቸው ወዲያውኑ በህይወታቸው ደስተኛ መሆን ይጀምራሉ።
ከካርታ እና ከዳማ መሰል ጨዋታዎች አንስቶ ገጸ ባህሪያትን በመላበስ እና ጠጠር በመወርወር እስከሚጫወቷቸው ጨዋታዎች ድረስ በመላው ዓለም ለዘመናት የሚታወቁ በርካታ የተለያዩ ጨዋታዎች አሉ። አፍሪካውያን ለበርካታ ክፍለ ዘመናት ጨዋታዎችን ሲጫወቱ እንደቆዩ የቅሪተ አካል ምርምር ግኝቶች ያረጋግጣሉ።
ጨዋታ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መብት ኮንቬንሽን በአንቀጽ 31 ውስጥ መደበኛ በሆነ መልኩ እንደሚከተለው ዕውቅና ሰጥቶታል፡- የህጻናት የማረፍ እና የመዝናናት እንዲሁም ለህጻኑ ዕድሜ አግባብ በሆነ ጨዋታ እና የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍ እና በባህላዊ ህይወት እና በጥበብ ውስጥ በነጻነት የመሳተፍ መብት።
ጨዋታ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ለህጻናት እና ለዕድገታቸው ልዩ ዕድሎችን የሚፈጥር ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው። የህጻናትን ደህንነት እና ዕድገት ለማጠናከር እንክብካቤ ሰጪዎች የሚከተሉትን ሦስት መርሆዎች መከተል እንዳለባቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡-
- ለህጻኑ ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጡ ግንኙነቶችን መደገፍ
- አንኳር የህይወት ክህሎቶችን ማጠናከር
- የጭንቀት ምንጮችን መቀነስ።
ጨዋታ ሦስቱንም ለመደገፍ የሚያስችል ዘዴ ነው። በጨዋታ አማካኝነት ህጻናት ጓደኝነቶችን ይመሰርታሉ፣ ግንኙነቶችን ይደራደራሉ፣ እንደ ቅናት፣ ንዴት እና ድብርት ስላሉ ስሜቶች ይማራሉ እንዲሁም ከተፈጥሮ እና በዙሪያቸው ካለው አካባቢ ጋር ይገናኛሉ። ጨዋታ ለአእምሮ፣ ለአካላዊ፣ ለማህበራዊ እና ለስሜት ደህንነት አስተዋጽዖ የሚያደርግ በመሆኑ ለህጻናት ዕድገት አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ጨዋታ እንክብካቤ ሰጪዎች ከልጆቻቸው ጋር ሙሉ በሙሉ መስተጋብር እንዲያደርጉ እና በጋራ እንዲደሰቱ ሁነኛ ዕድልን ይፈጥራል።
በጨዋታ አማካኝነት ህጻናት፡-
- በራስ የመተማመን ስሜታቸውን ያዳብራሉ እንዲሁም ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት እና ክብር ይጨምራል
- ማህበራዊ ክህሎቶቻቸውን፣ ቋንቋቸውን እና የመግባባት ችሎታቸውን ያዳብራሉ
- ሌሎች ሰዎችን እና አካባቢያቸውን መንከባከብን ይማራሉ
- አካላዊ ክህሎቶችን ያዳብራሉ እንዲሁም አካላዊ ጤናቸውን ያሻሽላሉ
- ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያዳብራሉ
- ስጋቶችን በመጋፈጥ፣ ችግሮችን በመፍታት እና አዳዲስ ሁኔታዎችን በማስተናገድ ጽናትን ይገነባሉ
ጨዋታ ህጻናት በቀላሉ እንዲማሩ የሚረዳ መንገድ ነው። ጨዋታ የህጻናትን አእምሯዊ፣ አካላዊ እና ማህበራዊ/የስሜት ዕድገት የሚያጠናክሩ የተለያዩ ይዘቶች አሉት። ጨዋታ የዕለት ተዕለት ህይወት አንድ አካል ሲሆን በት/ቤት የሚኖረው የመማር ችሎታ በጣም እንደሚሻሻል ጥናቶች ያሳያሉ።
የአእምሮ ዕድገት
የህጻናትን የአእምሮ ዕድገት የሚያዳብሩ በርካታ የተለያዩ ጨዋታዎች አሉ። የሸክላ ማማ እየገነባ ያለ አንድ ህጻንን አስቡ። ማማውን ለመገንባት ማማውን በሚያቅድበት ወቅት ህጻኑ የማልማት እና የማቀድ ክህሎቶቹን ይጠቀማል። በተጨማሪም ህጻኑ ማማው በሚደረመስበት ወቅት ሀዘንን መቆጣጠርን ይማራል። ህጻኑ እንቅስቃሴዎቹን እስኪካንባቸው ድረስ መሞከሩን ይቀጥላል። ይህን በማድረግም ችግር የመፍታት ክህሎቶችን ይማራል። የህጻናትን የአእምሮ ዕድገት የሚያጠናክሩ ሌሎች የጨዋታ እንቅስቃሴዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
- አሻንጉሊቶችን መደርደር እና እንቆቅልሾችን መፍታት ህጻናት ቁጥሮችን እና ቅርጾችን እንዲማሩ ያግዛል
- የካርታ ጨዋታዎች እና ዳማ ነክ ጨዋታዎች የህጻናትን የመማር ባህሪ እና የትምህርት ዕድገት ለማሻሻል ይረዳል
- የራሳቸውን ጨዋታዎች መፍጠር ህጻናት በዙሪያቸው ላለው ዓለም ትርጓሜ እንዲሰጡ፣ ከዚያ ጋር እንዲቀራረቡ እና እንዲያስሱት ይረዳል
- መዝሙሮችን መማር እና መዘመር የቋንቋ ዕድገትን ለማሻሻል ይረዳል
አካላዊ ዕድገት
ጨዋታ የህጻናትን አካላዊ ዕድገት በከፍተኛ ሁኔታ ያጠናክራል። ለምሳሌ ትንሽ ዕድሜ ላይ ያሉ ህጻናት አሻንጉሊቶችን በሚገፉበት እና በሚጎትቱበት ወቅት እንዲሁም ትናንሽ ነገሮችን በሚያነሱበት ወቅት መሰረታዊ የመንቀሳቀስ ችሎታቸውን ያጠናክረዋል። በዕድሜ ተለቅ ያሉ ህጻናት ደግሞ በመወርወር፣ በመቅለብ፣ በመንጠላጠል እና በመጻፍ አካላዊ እና የመንቀሳቀስ ችሎታዎቻቸውን ያዳብራሉ። አካልን (እግሮችን፣ ክንዶችን፣ እጆችን እና ጡንቻዎችን) በቀላሉ ማንቀሳቀስን መልመድ “የመንቀሳቀስ ክህሎቶች” ተብሎ ይጠራል። የዛፍ ግንድ ቁራጮችን ወይም ድንጋዮችን ተጠቅመው ትናንሽ መረማመጃ ጉብታዎችን በመስራት እና በአንድ ጊዜ አንዱን ብቻ በአንድ እግራቸው እንዲረግጡ ህጻናትን በመጠየቅ የመንቀሳቀስ ክህሎቶችን ዕድገት በቀላሉ ማጠናከር ይቻላል። በተመሳሳይ መልኩ ህጻናት ሚዛን የመጠበቅ ክህሎቶቻቸውን እንዲፈትኑ ሁለት የግንድ ቁራጮች ላይ ጣውላ በማስቀመጥ የህጻናትን ሚዛን የመጠበቅ ችሎታ ማሻሻል ይቻላል።
ምሳሌ፡- ናዴጌ ዕድሜዋ ስድስት ዓመት ነው። ዕድሜዋ ሁለት ዓመት አካባቢ እያለ ነበር ከጎዳና ላይ የተገኘችው። ማነቃቂያ አልተደረገላትም ነበር ስለዚህ የምትራመደው አጎንብሳ ነበር እንዲሁም ሚዛን የመጠበቅ ችሎታዋ በጣም ደካማ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ትወድቅ ነበር እና የምትራመደውም እንደ የአንድ ዓመት ህጻን ነበር። ከዚያ የአደራ ቤተሰብ እናቷ ከእሷ ጋር የምትጫወተው ጨዋታ ፈጠረች፡- ጭንቅላቱ ላይ ለረጅም ሠዓት ቅርጫት ማስቀመጥ የሚችለው ማን ነው የሚል። ምንም እንኳን የአደራ ቤተሰብ እናቷ ይህን በቀላሉ ማድረግ ብትችልም አብዛኛውን ጊዜ አውቃ ቅርጫቱን ትጥለው እና ሁለቱም እየተለማመዱ ይስቁ ነበር። ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ናዴጌ ቅርጫቱ ሳይወድቅባት ረጅም ርቀት በኩራት መራመድ የቻለች ሲሆን አሁን ሰውነቷን ቀጥ አድርጋ ግርማ ሞገስ ባለው መልኩ መራመድ ጀምራለች። የጨዋታ እንቅስቃሴ በመሆኑ ናዴጌ መሞከሯን አላቋረጠችም። በቁጣ እየተነገራት ወይም ደግሞ ሰውነቷን ቀጥ እንድታደርግ በተደጋጋሚ እየተነገራት ቢሆን ኖሮ ይህንን ፈጽሞ አትለምድም ነበር።
ማህበራዊ/የስነ-ልቦና ዕድገት
በጨዋታ አማካኝነት ማህበራዊ መስተጋብሮች ወደ ግንኙነቶች ይቀየራሉ። በጨዋታ ዙሪያ በሚደረገው መስተጋብር አማካኝነት ጨዋታ በእንክብካቤ ሰጪ እና በህጻን ልጅ መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል። ከልጆቻቸው ጋር በመጫወት እንክብካቤ ሰጪዎች ህጻኑን ይበልጥ እያወቁት ይመጣሉ፤ ይህም በእንክብካቤ ሰጪው እና በህጻኑ መካከል ያለውን ፍቅር የተሞላበት ግንኙነት እና መስተጋብር እያጠናከረው ይመጣል።
ከሌሎች ሰዎች አጠገብ አና ከሌሎች ሰዎች ጋር መጫወት፣ አዋቂዎች የሚያደርጉትን ነገር አስመስሎ ማድረግ እና የአዋቂ ሥራዎችን እና ተግባራትን መለማመድ የህጻናትን ማህበራዊ እና ስነ-ልቦናዊ ዕድገት ያጠናክራል። በተጨማሪም እንደ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ የማስመሰል ጨዋታ እና ደንቦችን መሰረት ያደረጉ ጨዋታዎች ያሉ እንቅስቃሴዎች ህጻናት ማህበራዊ እና የስነ-ልቦና ዕድገት እንዲያመጡ ይረዳል። ጨዋታ ላይ የሚዳብሩ ክህሎቶች በኋለኛው ህይወት ውስጥ የሥራ ክህሎቶች ይሆናሉ።
ፈጠራን በመጠቀም ችግሮችን የመፍታት ክህሎቶችን ለማዳበር ጨዋታ አስፈላጊ ነው። ፈጠራን በመጠቀም ችግሮችን የመፍታት ጥሩ ክህሎቶች ያሏቸው ህጻናት እና ወጣቶች የዕለት ተዕለት ችግሮችን እና ተግዳሮቶችን ማስተዳደር እና መቋቋም ላይ ይበልጥ ጎበዝ እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህም በፍጥነት በመለወጥ ላይ ባለው በዓለማችን ውስጥ አስፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣት ላይ ያለ ክህሎት ነው።
ምሳሌ፡- ሁለት ጓደኛሞችን አስቡ፡- ጋሂኪ እና ማዚምፓካ ይባላሉ፤ ዕድሜያቸው ሰባት ዓመት ነው። የማስመሰል ጨዋታ ፈጥረዋል፡- ጋሂኪ ፖሊስ ነው እና መኪናውን ከመጠን በላይ በፍጥነት ስላሽከረከረ ማዚምፓካን ለመያዝ ጥረት እያደረገ ነው። በተደጋጋሚ ስለ ህጎቹ ይወያያሉ እንዲሁም ይከራከራሉ፤ ስለዚህ ሁለቱም ሕጎች ላይ መደራደርን፣ ሰምምነት ላይ መድረስን እንዲሁም ከሁኔታዎች ጋር ራስን ማስማማትን ይማራሉ። ስለዚህ ቀላል የማስመሰል ጨዋታን በመጫወት ህጻናት በአዋቂነት ወቅት ወሳኝ የሆኑ ችሎታዎችን ይማራሉ እንዲሁም ይዳስሳሉ።
አስታውሱ፣ ጨዋታ ደስታ ነው። እያንዳንዱ ህጻን የሚያድገው በራሱ መንገድ እና በራሱ ጊዜ ነው። ስለዚህ ልጃችሁ ላይ ግፊት ላለማድረግ ወይም ልጃችሁን እና ችሎታዎቹን ከሌሎች ልጆች ጋር ላለማወዳደር ሞክሩ።
ለህጻናት ዕድገት ጥሩ የሆኑት እንዴት ያሉት ጨዋታዎች ናቸው?
ጨዋታዎች የተለያዩ ይዘቶች ሊኖሯቸው ይችላሉ። ማንኛውም ይዘት ያለው ወይም ማንኛውም ዓይነት ጨዋታ ለህጻናት ዕድገት ጠቃሚ ነው። ህጻናት በአሻንጉሊቶች፣ በልብሶች፣ በካርቶኖች፣ በቀለም ወይም በአካባቢያቸው ውስጥ በአሸዋ እና በውሀ ሊጫወቱ ይችላሉ። የተለያዩ የጨዋታ ዓይነቶች እያንዳንዳቸው ህጻናት የተወሰኑ ችሎታዎችን እንዲያዳብሩ ይረዳሉ።
ለምሳሌ፡-
- በአካባቢ ውስጥ በአሸዋ እና በውሀ መጫወት ህጻናትን ከሂሳብ እና ከሳይንስ ጋር ያስተዋውቃቸዋል፤ ለምሳሌ ምን ፈሳሽ እና ምን ጠጣር እንደሆነ እና ነገሮችን እንዴት በዕቃዎች እና በሳጥኖች መለካት እንደሚቻል በመማር
- ስዕሎችን መሳል ወይም ቀለም መቀባት፣ በአሻንጉሊቶች መጫወት እና የተለያዩ ልብሶችን በመልበስ መጫወት የህጸናትን የፈጠራ ችሎታ፣ ምናብን የመጠቀም ችሎታ እንዲሁም ስሜትን የመግለጽ ችሎታ ያጠናክራል
- ተገጣጣሚ መጫወቻዎች እና የተለያዩ ቅርጾች ያሏቸው አሻንጉሊቶች የተለያዩ ቅርጾችን የማወቅ እና ነገሮችን በአግባቡ የመደርደር ችሎታን ያጠናክራል፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብን ያዳብራል፣ ወዘተ።
- የኳስ ጨዋታዎችን መጫወት፣ መደነስ፣ መሮጥ፣ መንጠላጠል፤ እነዚህ እንቅስቃሴዎች በሙሉ አካላዊ ክህሎቶችን፣ ጥንካሬን፣ የመተጣጠፍ ችሎታን እና ሰውነትን አቀናጅቶ የመጠቀም ክህሎቶችን ለማዳበር ይረዳሉ።
- መዝሙሮችን መዘመር እና መደነስ አብዛኛውን ጊዜ የጨዋታ አንድ አካል ናቸው። ሰውነትን የመቆጣጠር ችሎታን እና በሁሉም እንቅስቃሴ ውስጥ ምትን የመጠበቅ ችሎታን ያጠናክራሉ።
አብዛኛውን ጊዜ ህጻናት ለመጫወት ብዙ አሻንጉሊቶች ሊኖሯቸው ይገባል የሚል እምነት አለ። ሆኖም ግን ህጻናት የራሳቸውን ምናብ እንዲጠቀሙ እና የራሳቸውን ጨዋታዎች እንዲፈጥሩ የሚያስችሉ መጫወቻዎች እያደጉ ሲመጡ ህይወትን እንዲያጣጥሙ እንደሚረዷቸው ጥናቶች ያሳያሉ። በዙሪያችን ካሉ ነገሮች መጫወቻዎችን መስራት የጨዋታ ሂደቱ አንድ አካል ነው። ያገለገለ የቆርቆሮ ጣሳ እና የተወሰነ ትርፍ ሽቦ መኪና ሊወጣቸው ይችላል። አሻንጉሊቶች ከቁርጥራጭ ጨርቆች እና ከቅርንጫፎች ሊሰሩ ይችላሉ። መጫወቻዎችን መሥራት ህጻናት በምናባቸው ነገሮችን መሳልን እና መገንባትን እንዲማሩ ይረዳል። ስለዚህ ህጻናት ጤናማ አንጎል እንዲያዳብሩ የሚያማርጡት ብዙ አሻንጉሊት አያስፈልጋቸውም። የሚያስፈልጋቸው የራሳቸውን ምናብ እና የፈጠራ ችሎታ እንዲጠቀሙ የሚያነሳሷቸው የተወሰኑ ቀላል መገልገያዎች ብቻ ናቸው።
ትንሽ ዕድሜ ላይ ያሉ ህጻናት ትልቅ ቦታ የሚሰጧቸው መጫወቻዎች ወረቀት እና ቀለም፣ ውሀ እና አሸዋ፣ ጭቃ፣ የአትክልት ስፍራ ወይም መናፈሻ፣ ድስት እና መጥበሻ፣ የእንጨት ማንኪያዎች እና ብሎኬቶች፣ አሻንጉሊቶች፣ ማየት የሚችሏቸው እንስሳት እና ነፍሳት፣ የተለያዩ ቅርጾች ያሏቸው ሳጥኖች፣ ለብሰው ሊጫወቱባቸው የሚችሏቸው አሮጌ ልብሶች ናቸው። ብዛት ካላቸው ውድ መጫወቻዎች ይልቅ ህጻናት የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲጠቀሙ የሚረዱ ጥቂት መጫወቻዎች (ራሳቸው እንደሚሰሯቸው የመጫወቻ ልብሶች እና መጫወቻዎች ያሉ) በጣም ትልቅ ዋጋ አላቸው።