ክፍለ ጊዜ 16/21

ገጽ 3/6 ባህላዊ የህጻናት ጨዋታዎች

ባህላዊ የህጻናት ጨዋታዎች

ጨዋታ ጊዜ ማሳለፊያ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ባህልን የማስተላለፊያ መሳሪያም ጭምር ነው። በአንድ ጨዋታ ውስጥ ያሉት ባህላዊ ይዘቶች ለህጻናት ስለ ባህላቸው ግንዛቤ ይሰጧቸዋል እንዲሁም ባህላዊ ማንነታቸውን ያጠናክሩላቸዋል።

በአፍሪካ ባህል ውስጥ የበለጸገ የጨዋታ ባህል እና የተለያዩ የመዝሙር ጨዋታዎች አሉ። ህጻናት በጨዋታዎች እና በመዝሙር ጨዋታዎች አማካኝነት ስለ ማህበራዊ ምህዳራቸው ዕውቀት ማግኘት እና እንደ መልካም ባህሪ፣ ሥነ-ምግባር፣ ጠንክሮ መስራት፣ ጽናት እና የአመራር ሚና መጫወት ያሉ ባህላዊ እሴቶችን ይማራሉ። ስለዚህ ባህላዊ ጨዋታዎች የአንድን ማህበረሰብ ባህል የሚገልጹ በመሆኑ ህጻናት በእነዚህ ባህላዊ ጨዋታዎች አማካኝነት ስለ ማህበረሰባቸው እና ስለ ባህላዊ እሴቶቻቸው ይማራሉ።

ባህላዊ ጨዋታዎች ህጻናት ባህላዊ ማንነታቸውን እንዲያዳብሩ እና ስለ ደንቦች እና እሴቶች በተዘዋዋሪ እንዲማሩ ስለሚረዷቸው ለህጻናት በጣም ጠቃሚ ናቸው። ይህም ስለራሳቸው ያላቸውን ጥቅም ያለኝ ሰው ነኝ የሚል ስሜት ያጠናክረዋል እንዲሁም ለወደፊቱ የአዋቂነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲጫወቱ ይረዳቸዋል።

ባህላዊ ጨዋታዎች ምንድን ናቸው?
በአፍሪካ ባህሎች ውስጥ የህጻናት ጨዋታዎች ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩት በአፍ/በቃል ነው። ባህላዊ ጨዋታዎች አብዛኛውን ጊዜ የግድ መከተል የሚያስፈልጉ የተወሰኑ ህጎች ያሏቸው አካላዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው። ፉክክር ሊኖርባቸው ይችላል እንዲሁም አንድ ተሳታፊ ዕውቅና፣ ደረጃ ወይም ክብር ለማግኘት ሊሳተፍባቸው ይችላል።

ባህላዊ ጨዋታ በህጻናት እና በወጣቶች የሚከናወን እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴው አብዛኛውን ጊዜ ሀገር በቀል መዝሙሮችን በመዘመር የታጀበ ነው። የልጅነት ባህል አንድ ወሳኝ አካል ነው። ባህላዊ ጨዋታዎች ለአዋቂዎች እንዲሁም ለህጻናት አዝናኝ እንዲሆኑ ተደርገው የተዘጋጁ ናቸው። የኬንያው ጨዋታ ንያማ-ንያማ-ንያማ፣ የጋናው አምፔ፣ የሩዋንዳው አጋታምባሮ ኩምዋና፣ የዝምባብዌው ኩዶዳ ወይም ታዋቂው ባህላዊ የአፍሪካ የህጻናት ጨዋታ ማምባ ለዚህ ምሳሌዎች ናቸው።

ንያማ-ንያማ-ንያማ፡-

የተሰበሰቡት ልጆች አንድ መሪ ይመርጣሉ። መሪውም “ንያማ-ንያማ-ንያማ” ብሎ በመጮህ ጨዋታውን ያስጀምራል፤ ይህም በስዋሂሊ ቋንቋ “ስጋ” ማለት ነው። ሌሎቹ ተጫዋቾች ዘለው መሪው ያለውን ይደግማሉ። ከዚያም መሪው የተለያዩ እንስሳትን ስም ይጠራል። የእንስሳው ስጋ ኬንያ ውስጥ (ወይም ጨዋታውን የምትጨወቱበት ሀገር ውስጥ) የሚበላ ከሆነ ሌሎቹ ተጫዋቾች ዘለው “ንያማ” ብለው ይጮሀሉ። መሪው ስጋው የማይበላ እንስሳ ስም ከጠራ ተጫዋቾቹ ሳይንቀሳቀሱ ባሉበት መቆም አለባቸው። አንድ ተጫዋች እንቅስቃሴ ካሳየ ከጨዋታው ይወጣል። አንድ ተጫዋች ብቻ ቀርቶ አሸናፊ እስከሚሆን ድረስ ጨዋታው ይቀጥላል።

ማምባ፡-

የተሰበሰበው ሰው በጨዋታው ቦታ ዙሪያ ድንበር ያሰምራል። ሁሉም ተጫዋች በጨዋታው ወቅት ከመስመሩ ውስጥ መቆም አለበት። አንድ ተጫዋች ማምባ እንዲሆን ይመረጣል። ማምባው እየተሯሯጠ ሌሎቹን ተጫዋቾች ለመያዝ ይሞክራል። አንድ ተጫዋች ሲያዝ የማምባውን ትከሻ ወይም ወገብ በመያዝ ከማምባው ጋር ይቀላቀላል። ሌሎች ተጫዋቾችን መያዝ የሚችለው የመጀመሪያው ማምባ ተጫዋች ብቻ ነው። ከማምባው ጋር የተያያዙት ተጫዋቾች ሌሎች ተጫዋቾች እንዳያልፉ በማድረግ ማገዝ ይችላሉ። አንድ ተጫዋች ብቻ ቀርቶ አሸናፊ እስኪሆን ድረስ ጨዋታው ይቀጥላል።

አምፔ፡-

የተሰበሰቡት ልጆች አንድ መሪ ይመርጡ እና ህጻናቱ ፊታቸውን ወደ መሪው መልሰው ግማሽ ክብ ሰርተው ይቆማሉ። መሪው ግማሽ ክብ ሰርተው ከቆሙት ልጆች ውስጥ መጀመሪያ ላይ ወዳለው አንድ ተጫዋች ፊቱን መልሶ ይቆማል። ሁለታቸውም አጨብጭበው ይዘላሉ። አንደኛውን እግራቸውን ወደፊት አድርገው እንደገና ይዘላሉ። ሁለታቸውም ወደፊት ያደረጉት ተመሳሳይ እግራቸውን ከሆነ መሪው ይወጣ እና ከተጫዋቹ ጋር ቦታ ይቀያየራል። ከዚያም አዲሱ መሪ ግማሽ ክብ ሰርተው ከቆሙት ልጆች ውስጥ ቀጥሎ ካለው ተጫዋች ጋር ያንኑ ደግሞ ያደርጋል።

ወደፊት ያደረጉት የተለያዩ እግሮቻቸውን ከሆነ መሪው ቦታው ላይ ይቆይ እና ወደሚቀጥለው ተጫዋች ይሄዳል። 

ኩዶዳ፡-

ተጫዋቾቹ ክብ ሰርተው ይቀመጡ እና መሀላቸው ላይ ጠጠር (ትናንሽ ድንጋይ) በጎድጓዳ ዕቃ ይቀመጣል። የመጀመሪያው ተጫዋች አንድ ጠጠር አየር ላይ ይወረውራል። ከዚያ ይኸው ተጫዋች የወረወረውን ጠጠር መልሶ ከመቅለቡ በፊት በተቻለው መጠን ብዙ ጠጠሮችን ለማንሳት ይሞክራል። ከዚያም የሚቀጥለው ተጫዋች ተራ ይሆናል። ብዙ ጠጠር የለቀመው ተጫዋች አሸናፊ ይሆናል።

አጋታምባሮ ኩምዋና፡-

ህጻናት ትይዩ ሆነው ክብ ሰርተው ይቀመጣሉ። ከመሀላቸው አንድ ሰው ተመርጦ የጨዋታው መሪ ይሆን እና የእጅ መጥረጊያ ሶፍት ወስዶ ማንም ሰው ሳያየው እጁ ውስጥ በደንብ አድርጎ ይደብቀዋል። ከዚያም ልጁ “የልጁ የእጅ መጥረጊያ ሶፍት የታለ” ብሎ እየጮኸ ክቡን ይዞረዋል፤ ሌሎቹ ልጆች ደግሞ “እዚያ ጋር ሲያልፍ አይተነዋል” ብለው ይመልሳሉ፤ ከዚያም የጨዋታው መሪ “ልታገኙት ትችላላችሁ?” ይላል። ከዚያም ሌሎቹ ልጆች “አአአአይይይይ” ይላሉ። መሪው በሚስጥር ከሆነ ሰው ኋላ ሶፍቱን/መሐረቡን ያስቀምጥ እና በፍጥነት ክቡን በሩጫ ይዞረዋል። መሪው ክቡን ዞሮ ሶፍቱን/መሐረቡን ያስቀመጠበት ቦታ ላይ ሲደርስ ሶፍቱ/መሐረቡ ከኋላው ያለው ሰው የጨዋታው መሪ ክቡን እየዞረ እያለ ካልነቃ ተሸናፊ ይሆናል። ከዚያም ተሸናፊው የጨዋታው መሪ ይሆን እና ጨዋታው ይቀጥላል።

መልመጃ – የልጅነት ጨዋታዎች

አዋቂ ተሳታፊዎችን 3-4 ሰዎች ባሉባቸው ቡድኖች ከፋፍሉ።

15 ደቂቃ፡- በልጅነታችሁ ትጫወቱት የነበረ አንድ ጨዋታ ለዩ እና ተወያዩበት

15 ደቂቃ፡- ሁሉም ቡድን የራሱን ጨዋታ እንዲያቀርብ እና ለሌሎቹ ቡድኖች እንዲያስተምር አድርጉ

የቡድን ውይይት

10 ደቂቃ

  • ጨዋታውን መጫወት ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረባችሁ?
  • ያዝናናል/አያዝናናም ብላችሁ የምታስቡበት ምክንያት ምንድን ነው?
  • ጨዋታ በልጆቻችሁ ላይ ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥራል?
  • ጨዋታን ማበረታታት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?