ክፍለ ጊዜ 16/21

ገጽ 4/6 የተለያዩ የጨዋታ ዓይነቶች

የተለያዩ የጨዋታ ዓይነቶች

በጥናቶች ውስጥ የህጻናት ጨዋታ የታቀደ ጨዋታ እና ያልታቀደ ጨዋታ ተብሎ በሁለት ይከፈላል (በጥናቶች ውስጥ ይህ የተደራጀ ጨዋታ እና ያልተደራጀ ጨዋታ ተብሎ ይጠራል)። የታቀደ ጨዋታ ማለት በአዋቂ የተዘጋጀ እና በተወሰነ ጊዜ እና ሁኔታ ውስጥ እንዲሁም አንዳንድ ህጎችን በመከተል የሚከናወን የጨዋታ ዓይነት ነው። ለምሳሌ እግር ኳስ የመጫወት ህጎች። ያልታቀደ ጨዋታ በህጻናት መካከል በነጻነት እና ሳይታቀድ የሚከናወን ጨዋታ ነው። ጨዋታው የታቀደ አይደለም እንዲሁም በራሱ ፍጥነት የሚሄድ እና ከህጻናት ምናብ እና ፈጠራ የሚመነጭ ነው። ለምሳሌ ህጻናት ስለ ጀግና ሰዎች ወይም ስላሳለፏቸው ነገሮች ታሪኮችን ሊፈጥሩ ይችላሉ።

የታቀደ እንዲሁም ያልታቀደ ጨዋታ ለህጻናት ዕድገት አስፈላጊ በመሆኑ እንክብካቤ ሰጪዎች ሁለቱንም ዓይነት ጨዋታ እንዲያበረታቱ ያስፈለጋል። ህጻናት የሚማሩት በጨዋታ በመሆኑ ከመጠን በላይ መጫወት የሚባል ነገር የለም።

የታቀደ ጨዋታ

የታቀደ ጨዋታ ማለት የተደራጀ የጨዋታ ዓይነት ነው እንዲሁም የሚከናወነው በተወሰነ ጊዜ እና ቦታ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሕጎቹን እና መቸቱን የሚወስኑት አዋቂዎች ናቸው። የታቀደ ጨዋታ የህጻናትን አንኳር የህይወት ክህሎቶች ዕድገት የሚያጠናክር በመሆኑ በብዙ መልኩ ለህጻናት ጠቃሚ ነው።
የታቀደ ጨዋታ በተለይም ደግሞ ድክ ድክ ለሚሉ ህጻናት እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ዕድሜ ላይ ላሉ ህጻናት ጥሩ ነው። ህጻናትን ከአዲስ እንቅስቃሴዎች ጋር ማስተዋወቂያ መንገድ ነው። በታቀደ ጨዋታ አማካኝነት አሻንጉሊቶችን በቅርጻቸው ወይም በቀለማቸው እንዲደረድሩ ድክ ድክ የሚሉ ህጻናትን ልታስተምሩ ትችላላችሁ እንዲሁም የካርታ ወይም ዳማ መሰል ጨዋታዎችን በማስተማር ወይም በመጫወት በዕድሜ ተለቅ ያሉ ልጆችን የአእምሮ ዕድገት ልታጠናክሩ ትችላላችሁ።

የሚከተሉት የታቀደ ጨዋታ ምሳሌዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡-

  • ለአንድ ህጻን ወይም ለተሰበሰቡ ህጻናት ተረት መንገር
  • ዳማ መሰል ወይም የካርታ ጨዋታዎች
  • እንደ ቅርጫት ኳስ፣ እግር ኳስ፣ ወዘተ ያሉ ጨዋታዎች
  • የዳንስ፣ የሙዚቃ ወይም የድራማ ክፍለ ጊዜዎች

ነገር ግን የታቀደ ጨዋታ አንድ አካል ተደርጎም ቢሆን ህጻናት በራሳቸው ነገሮችን እንዲሞክሩ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል። ለምሳሌ ድክ ድክ ለሚል ልጃችሁ አንዳቸው አንዳቸው ውስጥ የሚገቡ ኩባያዎችን ከሰጣችሁት መደራረብ የሚችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች እንዲሞክር ጊዜ ስጡት። በተጨማሪም የታቀደ ጨዋታ የታጠቡ ልብሶችን እንደማጣጠፍ ካለ የዕለት ተዕለት ተግባር ጋር ሊቀናጅ ይችላል። ህጻኑ የታጠቡትን ልብሶች በቀለም ለይቶ እንዲደረድር ወይም ሁለት እግር ካልሲዎችን እንዲያጣምር አድርጉ። በተጨማሪም ህጻኑን ቤት ውስጥ በሚንቀሳቀስበት ወቅት እንደ ካንጋሮ እየዘለለ ብቻ እንዲንቀሳቀስ በመጠየቅ ወይም ምግብ እያበሰላችሁ እያላችሁ ሙዚቃ ሲኖር የመደነስ እና ሙዚቃው ሲቆም የመቆም ጨዋታ እንዲጫወቱ በማድረግ የህጻናትን አካላዊ ዕድገት ማጠናከር ትችላላችሁ።

ያልታቀደ ጨዋታ

ያልታቀደ ጨዋታ ከታቀደ ጨዋታ ይለያል። ህጻኑ በሠዓቱ ያለውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የሚከናወን የጨዋታ ዓይነት ነው። ነጻ ጨዋታ የታቀደ ሊሆን አይችልም ።በህጻኑ ምናብ የሚወሰን ነው።

ባልታቀደ ጨዋታ አማካኝነት ህጻናት በቡድን መሥራትን፣ መጋራትን፣ መደራደርን፣ ግጭቶችን መፍታትን እና ውሳኔ መወሰንን ይማራሉ እንዲሁም ይለማመዳሉ። አዋቂዎች የሌሉባቸው ጨዋታዎች ላይ ህጻናት የአዋቂዎችን ሕጎች እና ስጋቶች መከተል ሳይኖርባቸው የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲሁም የአመራር እና የቡድን ክህሎቶቻቸውን ለማዳበር ነጻነቱ ይኖራቸዋል።

የሚከተሉት ያልታቀደ ጨዋታ ምሳሌዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡-

  • አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው ዕቃዎችን፣ ሸክላዎችን እና ብርድልብሶችን በመጠቀም ቤት እንደመስራት ያሉ የፈጠራ ጨዋታዎች
  • የተለያዩ ልብሶችን እና ብርድ ልብሶችን ለብሰው መጫወት
  • እንደ አዋቂ እንዲሁም እንደህጻን በመምሰል የተለያዩ ገጸ ባህሪያትን በመላበስ የማስመሰል ጨዋታ መጫወት
  • እንደ የጥበብ ወይም የሙዚቃ ውድድር ያሉ የፈጠራ ችሎታን የመጠቀም ጨዋታዎች
  • የመጫወቻ ስፍራዎችን እንደማሰስ እና በውሀ፣ በአሸዋ፣ በጭቃ፣ በተክሎች፣ ወዘተ እንደመጫወት ያሉ የተለያዩ ከቤት ውጭ የሚደረጉ ጨዋታዎች

በተለይም ደግሞ ከቤት ውጭ የሚደረግ ጨዋታ ህጻናት ስለአካባቢያቸው ብዙ ሊማሩበት እና ሙሉ ሰውነታቸውን በማሰራት የመንቀሳቀስ ክህሎቶቻቸውን ሊያዳብሩ የሚችሉበት በመሆኑ ለህጻናት ጠቃሚ ነው።

ምንም እንኳን ያልታቀደ ጨዋታ የሚከናወነው ህጻኑ በሚፈልገው መልኩ ቢሆንም እንክብካቤ ሰጪዎች በጨዋታው ውስጥ መሳተፍ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ህጻናት ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ (ሳጥን ውስጥ ወዳሉት አሻንጉሊቶች ወይም ልብስ በመልበስ ለመጫወት ወደ ቁም ሳጥኑ) እንዲሄዱ የሚጠቁማቸው ሰው ያስፈልጋቸዋለ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ባልተደራጀ ጨዋታ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፉ ትንሽ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል፡- “ልብስ የመልበስ ጨዋታ ብትጫወትስ?” “ዛሬ ምንድነው መሆን የምትፈልገው?” “ይህንን መጫወቻ ለምን መጠቀም ይቻላል?”

የጨዋታ ባህሪን የሚመለከቱ እይታዎች

ኃላፊነት ያለብን አዋቂዎች እንደመሆናችን መጠን ጥሩ የጨዋታ ባህሪን እናበረታታለን። የምናበረታታቸው አንዳንድ ጨዋታዎች አሉ የማናበረታታቸውም አንዳንድ ጨዋታዎች አሉ።

አዎንታዊ እሴቶች (ለምሳሌ መደራደር እና ተቀናጅቶ መስራት) በተግባር የሚታዩባቸው ጨዋታዎች አብዛኛውን ጊዜ በአዋቂዎች ይበረታታሉ። ነገር ግን አሉታዊ ነው ተብለው የሚታሰቡ እና/ወይም አዋቂዎች ላይ ጭንቀት የሚፈጥሩ ጨዋታዎች ቦታ አይሰጣቸውም። እነዚህ ጨዋታዎች በጣም ፈታኝ፣ ኃይል የተሞላባቸው ወይም ምንም ዓላማ የሌላቸው ጨዋታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ጭቃ ላይ እንደመጫወት፣ እንደ መደባደብ፣ ግጭቶችን ወይም መሞትን እንደማስመሰል ያሉ ጨዋታዎች ማለት ነው።

ነገር ግን አንዳንድ አጨዋወቶችን በምንከለክልበት መንገድ ላይ ማተኮር አስፈላጊ ነው። ከመረጋጋት እና ለስለስ ያሉ ቃላትን ከመጠቀም በተጨማሪ የሰውነታችን አኳኋን የሚያስተላልፈውን መልዕክት እንዲሁም ህጻናቱን የምንመለከትበትን መንገድ ማስተዋል አለብን፣ ወዘተ።

ህጻናት እንደ የቤት ውስጥ ጥቃት ያሉ በጣም አስከፊ ወይም አሰቃቂ ክስተቶችን ያሳለፉ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ያጋጠማቸውን ነገር በሚጫወቱት ጨዋታ ውስጥ ይደግሙታል፤ ይህም የማገገም ሂደታቸው አንድ አካል ነው። ይህን አጋጣሚ እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም ስላጋጠማቸው ነገር ልታዋሯቸው፣ አመራር ልትሰጧቸው እና ያሳለፉትን ተሞክሮ ይበልጥ አዎንታዊ ወደሆነ ታሪክ ልትቀይሩት ትችላላችሁ። እዚህ ላይ አዋቂ እንደመሆናችሁ መጠን እገዛ ካላደረጋችሁላቸው ኃይል በተሞላበት መልኩ መጫወታቸውን ሊቀጥሉ እና ያዩትን ነገር ካለማቋረጥ ደግመው ሊያደርጉ ይችላሉ።

ምሳሌ፡- ኢማኩሌ ዕድሜዋ አምስት ዓመት ነው። ሌሎች ሴት ልጆች ላይ በጣም አምባገነን እና ቂመኛ ናት እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ እንክብካቤ ሰጪዎቿ ላይ የምትናደድ ከመሆኑም በላይ በተለይም ደግሞ ወንዶችን ትፈራለች። ሁኔታዎችን በሙሉ ለመቆጣጠር ትሞክራለች። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንድ ምሽት ላይ እናቷ በዘራፊዎች ጥቃት ሲፈጸምባት አይታ ነበር። አንድ ቀን የአደራ ቤተሰብ እናቷ ራሳቸው የሚሰሯቸውን ትናንሽ አሻንጉቶች በመጠቀም የቴአትር ጨዋታ እንጫወት ብላ ልትጋብዛት ወሰነች። በዚህ ጨዋታ ላይም ታሪክ ፈጥረው የዘረፋውን ሁኔታ ብዙ ጊዜ ደጋግመው ተወኑት። እየተጫወቱ እያሉ የአደራ ቤተሰብ እናቷ ዘረፋው በተከሰተበት ወቅት ኢማኩሌ ምን እንደተሰማት እና እናቷ ምን እንደተሰማት ደጋግማ ታወራት ነበር። ከዚያም እናትየውን እና ልጅቷን ጎረቤቶች አገዟቸው እና ዘራፊዎቹን አባረሯቸው የሚል ታሪክ ፈጠሩ። በዚህም ቀስ በቀስ ኢማኩሌ ስለ ሁኔታው ያላት ትውስታ አስፈሪነቱ እየቀነሰ እየቀነሰ ሊመጣ ችሏል እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር ባላት ግንኙነት ውስጥም ይበልጥ የተረጋጋች እና ይበልጥ የሰከነች ለመሆን ችላለች።

ጨዋታ ጥቅም የሚያስገኘው ህጻናት ረዘም ላለ ጊዜ በርካታ የተለያዩ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ ሲቆዩ ነው። ስለዚህ ከአንዳንድ ጨዋታዎች ይልቅ ሌሎች ጨዋታዎችን የምናበረታታው ለምንድን ነው? አዋቂዎች ጎጂ ናቸው ብለው ከሚያስቧቸው ጨዋታዎች ህጻናት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ?

የቡድን ውይይት

የጨዋታ ባህሪዎችን በሚመለከቱ አስተሳሰቦች ላይ የሚደረግ ውይይት

    • አዋቂ እንደመሆናችን መጠን ልጆቻችን ለሚጫወቷቸው ጨዋታዎች የምንሰጠው ምላሽ ምን ዓይነት ነው?
    • የምናበረታታቸው የጨዋታ ዓይነቶች እና ሌሎች ደግሞ የማናበረታታቸው የጨዋታ ዓይነቶች አሉ?
    • ህጻናት ጨዋታቸውን በምናስቆምበት ወቅት የሚሰጡት ምላሽ እና የሚሰማቸው ስሜት ምን ዓይነት ነው?
    • ከአንዳንድ የጨዋታ ዓይነቶች በላይ ለሌሎች የጨዋታ ዓይነቶች ዋጋ የምንሰጠው ለምንድን ነው?
    • ልጆቻችን ይበልጥ የመጫወት ዕድሎችን ማግኘት እንዲችሉ ምን ማድረግ እንችላለን?

    ጨዋታ ለምን አስፈላጊ ነው የሚለውን በተመለከተ ህጻናት ያላቸው አመለካከት በጣም የተለየ ነው። ለምን መጫወት እንደሚወዱ እና አዋቂዎች ጨዋታቸውን ሲያስቆሙባቸው ምን እንደሚሰማቸው ጠይቋቸው።