ክፍለ ጊዜ 18/21

ገጽ 3/4 ርዕስ ለ፡- የማህበረሰብ ስብሰባዎችን ማቀድ እና ማከናወን

ርዕስ ለ፡- የማህበረሰብ ስብሰባዎችን ማቀድ እና ማከናወን

ርዕስ ለ ከ5-15 ሰዎችን ያካተቱ የአካባቢ የቡድን ስብሰባዎችን ማድረግ የምትችሉበትን ማዕቀፍ ይሰጣችኋል። ይህ ተጨባጭ ማዕቀፍ በማህበረሰቡ ውስጥ ለምታደርጉት የመጀመሪያ የቡድን ስብሰባ እንደ መመሪያ ያገለግላችኋል።

አስፈላጊ ከሆነ ከአንድ በላይ በሆኑ ቡድኖች ልትጀምሩ ትችላላችሁ። አሰልጣኝ ከሆነ ባልደረባችሁ ጋር እንድትሰሩ እና (ቢቻል) አንዳችሁ ወንድ እንድትሆኑ እንመክራለን። ከፌርስታርት ስልጠና ያገኛችሁትን ልምድ እንዲሁም የራሳችሁን ሀሳቦች ተጠቀሙ (ይህ ክፍለ ጊዜ የራሳችሁን ሥራ እንድትሰሩ የሚያነሳሳ ነው)።

በማህበረሰቡ ውስጥ ካሉ አስፈላጊ ሰዎች የሚሰጥ ድጋፍ ማመቻቸት

የመጀመሪያውን የማህበረሰብ ስብሰባ ከማዘጋጀታችሁ በፊት በአካባቢው ያሉትን ትስስሮች ብትመለከቱ እና ሌሎች ሰዎች በፕሮጀክቱ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዲኖራቸው ብታደርጉ ጥሩ ነው። በአካባቢው ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለው እና የሚደግፋችሁ ማን ነው ብላችሁ ታስባላችሁ? እነዚህ ሰዎች የሰፈር አዋቂዎች፣ የሃይማኖት አመራሮች፣ ማህበራዊ ሰራተኞች ወይም በሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

እባካችሁ በመደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ የማህበረሰብ ትስስሮች ውስጥ ያሉ ቁልፍ ሰዎችን የያዘ ዝርዝር አዘጋጁ፡-

ስለ አባቶች ህዝቡ ባለው አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉት ሰዎች እነማን ናቸው?
ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ግብ ላይ የሚሰሩት የትኞቹ ቡድኖች ናቸው (ሃይማኖታዊ፣ ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ወዘተ)?
የማህበረሰብ ስብሰባ ከማዘጋጀታችሁ በፊት መደበኛ ባልሆነ መልኩ ማንን ታነጋግራላችሁ?
ዕቅዳችሁን እንዴት ታቀርባላችሁ?

አባቶችን ለማጠናከር ከእናንተ ጋር እንዲሰሩ ሀሳብ አቅርቡላቸው። ስብሰባዎችን በማዘጋጀት እና ስብሰባዎች ላይ በመገኘት፣ ተሳታፊዎችን በመጋበዝ እና በህዝቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር ሊያግዟችሁ ይችላሉ። በተጨማሪም ይህን ማድረግ ለመጀመሪያው የማህበረሰብ ስብሰባ ወንዶችን ብቻ መጋበዝ ወይም ደግሞ አባቶች እና እናቶች ያሉባቸው ቅልቅል ቡድኖችን መጋበዝ እንደሚሻል ለመወሰን የሚረዳ ሀሳብ ይሰጣችኋል።

በማህበረሰባችሁ ውስጥ የቡድን ውይይቶችን ማድረግ የሚቻልበት መንገድ
አሰልጣኞች እንደመሆናችሁ መጠን በአካባቢ ማህበረሰብ ስብሰባዎች ላይ ልጆቻቸው ህይወታቸውን ሙሉ አዎንታዊ ዕድገት እንዲኖራቸው አባቶች አስፈላጊ ስለመሆናቸው ግንዛቤ ለመፍጠር መሥራት ትችላላችሁ። የቡድን ውይይቶች ላይ ተሳታፊዎችን ማነሳሳት ትችላላችሁ እንዲሁም አባቶች በንቃት እንዲሳተፉ ማድረግን በተመለከተ የራሳቸውን ሀሳቦች እንዲያቀርቡ ማነሳሳት እና ሀሳቦቻቸውን ማዳበር ትችላላችሁ። የራሳችሁን ተሞክሮ እና ዕውቀት ተጠቀሙ። የተወሰኑ ምክሮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-

የቡድን ስብሰባ መጀመር

ተገቢ ነው ብላችሁ በምታስቡት መሰረት የሚወሰን ሆኖ አንድ የቡድን ስብሰባ ከሁለት እስከ ሦስት ሠዓታት ይወስዳል።

አንድን የቡድን ውይይት አባቶች በባህሉ መሠረት ያሏቸውን የሥራ ድርሻዎች እና ይህም ወደ ከተሞች ሲመጡ እንዴት እንደተቀየረ በመግለጽ ልትጀምሩ ትችላላችሁ። የሚከተለው እንዴት መጀመር እንደምትችሉ የሚያሳይ ምሳሌ ነው (የስብሰባውን አጀንዳ እና ዓላማ ለመግለጽ የራሳችሁን ቃላት መጠቀም ትችላላችሁ)፡-

“ዛሬ እዚህ ስለተገኛችሁ እናመሰግናለን። ወደዚህ ስብሰባ እንድትመጡ የጠየቅኳችሁ ልጆቻቸውን በመንከባከብ እንዲሳተፉ በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ አባቶችን መደገፍ ስላለብን ነው። በከተሞች ውስጥ ሥራ አጥ ሆኖ መኖር ለአባቶች ህይወትን ከባድ አድርጎባቸዋል፤ የእነሱ እንክብካቤ ደግሞ ለህጻናቶቻችን እና ለወጣቶቻችን በጣም አስፈላጊ ነው።

በመንደሮች ውስጥ እንኖር በነበረበት ወቅት አባቶች ብዙ ስልጣን ነበራቸው። ለቤተሰባቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ያሟሉ ነበር እንዲሁም ጥበቃ ያደርጉላቸው ነበር። ባህላችን እና ታሪካችንም ከአንድ ትውልድ ወደሚቀጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ ያደርጉ ነበር። አዋቂ ወንዶች ወንድ ልጆችን ወደ አዋቂነት የማሸጋገር ኃላፊነት ነበራቸው እንዲሁም በዕድሜ ተለቅ ያሉ ወንዶች ለልጆቻቸው እና ለወጣቶች የተከበሩ መሪዎች እና አለማማጆች ነበሩ። ነገር ግን ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ግብርና መሥራት አቁመው በከተማ መኖር ሲጀምሩ በርካታ አባቶች ቤተሰባቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት ሥራ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ምንም እንኳን ይህ የእነሱ ጥፋት ባይሆንም ብዙ ሀፍረትን የፈጠረባቸው በመሆኑ በርካታ አባቶች ተስፋ ሊቆርጡ፣ ፍቺ ሊፈጽሙ ወይም ቤተሰባቸውን እና ልጆቻቸውን ጥለው ሊሄዱ ችለዋል። አብዛኛውን ጊዜ የሚሰማቸውን ስቃይ መቋቋም የማይችሉት ከመሆኑ የተነሳ አብዛኞቻቸው የአልኮል ሱሰኛ ይሆናሉ ወይም ዕጾችን ያለአግባብ መጠቀም ይጀምራሉ። ይህም ልጆቻችንን አደጋ ላይ ይጥላቸዋል። በማህበረሰባችን ውስጥ ሁላችንም አባቶቻችንን ለማጠናከር ተጋግዘን መሥራት አለብን።

ለእናንተ የማስተላልፋቸው ሁለት መልዕክቶች አሉኝ፡- ምንም የሚያሳፍር ምክንያት የለም፤ ማንኛውም አባት ሥራ አጥ መሆኑ የእሱ ጥፋት አይደለም! ሌላኛው መልዕክት ደግሞ የሚከተለው ነው፡- አንድ አባት ለቤተሰቡ  መተዳደሪያ የገንዘብ ምንጭ መሆን የማይችል ቢሆንም እንኳን ፍቅሩ እና ትኩረቱ ልጆቹ በህይወት ውስጥ ምን ያህል ጥሩ ሁኔታ ውስጥ ይሆናሉ የሚለውን በመወሰን ረገድ ከምንም ነገር በላይ ወሳኝ ነው! በዚህ ስብሰባ ላይ እንድትሳተፉ የጋበዝኳችሁም ለዚህ ነው፡- በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ አባቶች ለቤተሰቦቻቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ እንዲገነዘቡ ልንረዳቸው እና መልሰው እንዲሳተፉ ልናደርጋቸው ስለምንችልበት መንገድ እንነጋገር። ለዚህም የባህሎቻችንን ጠንካራ ጎኖች እንጠቀማለን። የራሴን ተሞክሮ ልንገራችሁ እና ከዚያ የእናንተን ተሞክሮ ደግሞ እጠይቃችኋለሁ።”

የቡድን ውይይት

አዎንታዊ እና አሉታዊ የአባትነት ተሞክሮዎች

የራሳችሁን የግል ምሳሌዎች ማግኘት። ተሳታፊዎች በትናንሽ የውይይት ቡድኖች የሚወያዩባቸው ጥያቄዎች።

የቡድን ውይይት 1

አንድ አባት ወይም አያት እንዴት የህጻናት ህይወት ውስጥ እንደተሳተፈ እና እንደተንከባከባቸው የሚገልጽ ምሳሌ ከራሳችሁ የልጅነት ህይወት ውስጥ ማግኘት ትችላላችሁ? አዎንታዊ ስልጣን የነበራቸውን አባቶች እና ፍቅራቸው እና እንክብካቤአቸው እንዴት ለልጆቻቸው በህይወታቸው ውስጥ እሴቶችን እና ጥንካሬን እንደሰጧቸው ማሰብ ትችላላችሁ?

የራሳችሁን ምሳሌ ካቀረባችሁ በኋላ ታዳሚዎቹን እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፡-

አሁን የእኔን ተሞክሮ ሰምታችኋል። እባካችሁ አጠገባችሁ ካሉ 3-4 ወንዶች ጋር ጥቂት ደቂቃዎችን አሳልፉ። ስለ መልካም አባትነት ሰላሏችሁ የራሳችሁ ትውስታዎች እና ምሳሌዎች ተወያዩ። ከዚያም የተወሰናችሁትን ያንን እንድታቀርቡ እጠይቃችኋለሁ።

ምሳሌዎችን በመስማት አምስት ደቂቃ አሳልፉ እና ምሳሌዎቹን ስላጋሩ አመስግኗቸው።

የቡድን ውይይት 2

ከዚያም ይህ ታላቅ ባህል እንዴት በከባድ ሥራ፣ በሥራ አጥነት እና በአሰቃቂ ተሞክሮዎች እንደተፈተነ የሚያሳይ አንድ የግል ምሳሌ ለቡድኑ ስጡ። የሚከተለው አንድ ምሳሌ ነው፤ እባካችሁ የራሳችሁን ምሳሌ ፈልጋችሁ ተጠቀሙ፡-

“አሁን ደግሞ ዝቅተኛ ደመወዝ እና ሥራ አጥነት የፈጠሩት ጫና አባቶች እንክብካቤ ከማድረጋቸው ጋር የተያያዙ ታላላቅ ባህሎቻችን ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ እንዳሳደረ እንመልከት። የእኔን ተሞክሮ ስንመለከት አባቴ ሥራ ለመሥራት ከቤተሰቡ ርቆ መሄድ ነበረበት፤ እናቴ ደግሞ ቀኑን ሙሉ በቤት ሠራተኝነት መሥራት ነበረባት። አባቴ በጣም ይናፍቀኝ ነበር፤ እና ቤት ሲመጣ  በጣም ደክሞት ይመጣ የነበረ ቢሆንም የሚያገኘው ገንዘብ ብዙ አልነበረም። ሁለቱም በጣም ጭንቀት ያለባቸው ከመሆናቸው የተነሳ አብዛኛውን ጊዜ ይጨቃጨቁ ነበር እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ አባቴ እናቴን ሲመታት አየው ነበር። ለእኛ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማሟላት ባለመቻሉ ያፍር ስለነበረ ውጭ ማምሸት እና መጠጣት ጀመረ። በመጨረሻም ቤተሰባችንን ጥሎ በመሄድ ሌላ ሚስት አገባ። አንዳንድ ጊዜ እንገናኝ እና እናወራ የነበረ ቢሆንም በጣም ይናፍቀኝ ነበር። ስለዚህ የአባት እንክብካቤ ለሚስቱ እና ለልጆቹ ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳለው እና ምንም እንኳን መንከባከብ የሚፈልጉ ቢሆንም ቤተሰባቸውን መንከባከብ ለወንዶች ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ።”

እባካችሁ በየቡድናችሁ እንደገና ተወያዩ እና ከራሳችሁ ህይወት ምሳሌዎችን በመስጠት አግዙኝ፡-

1.ልጅ እያላችሁ አባታችሁ ያጋጠሙት ተግዳሮቶች ምን ነበሩ?

2.ይህ ስለ አባትነት እናንተ ያላችሁን አስተሳሰብ በምን መልኩ ቀርጾታል?

3.በማደግ ላይ እያላችሁ እና ወጣት እያላችሁ ከአባታችሁ ያላገኛችሁት አመራር እና እንክብካቤ ምንድን ነው?

በአካባቢው አባቶች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለይታችሁ አስቀምጡ
“አሁን አባቶች ለቤተሰባቸው እና ለልጆቻቸው ደህንነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ አውቀናል።

እባካችሁ በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉትን ተግዳሮቶች እንድገነዘብ አግዙኝ። በትናንሽ ቡድኖች (ከአራት እስከ ስድስት ሰዎች) ተከፋፍላችሁ በሚከተለው ጥያቄ ላይ እንድትወያዩ እጠይቃለሁ፡- በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ አባቶችን በልጆቻቸው ህይወት ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚከለክሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

እባካችሁ አባቶች ከልጆቻቸው ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳይኖራቸው የሚከለክሉ ነገሮችን በተመለከተ ሦስት ምሳሌዎችን አግኙ። ከዚያም እያንዳንዱ ቡድን ሀሳቡን ያቀርብልናል።”

ቡድኖቹ እንደ ተግዳሮት የሚያዩአቸውን ነገሮች ካቀረቡ በኋላ ግልጽ በሆነ፣ የማወቅ ጉጉት ባለበት እና እንደገባችሁ በሚያሳይ መልኩ ምላሽ ስጡ። ብዙ ተስፋ መቁረጥ፣ ንዴት እና ጥላቻ ያለበት ንግግር ልትሰሙ ትችላለችሁ። ራሳችሁ መጥፎ ስሜት ውስጥ ሳትገቡ ለእነዚህ ስሜቶች እውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው። እንደገባችሁ በሚያሳይ መልኩ ምላሽ ስጡ፡- “የምትሉት ነገር ገብቶኛል፤ ይህ እውነትም አስቸጋሪ ነው”፣ ወይም “ይህ አባት ተስፋ መቁረጡ ምንም አይገርምም።

የአባት ተሳትፎን የሚመለከቱ አዎንታዊ እይታዎችን ከማቅረባችሁ በፊት እረፍት ውሰዱ

ይህ ጊዜ እረፍት ለመውሰድ እና ሊሰሩ በሚችሉ ስራዎች ዙሪያ ውይይት እንዲያደርጉ ታዳሚዎቹን ለመጠየቅ ለመዘጋጀት ጥሩ ጊዜ ነው፡-

አባቶች ስለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች የምታስቡትን /ሀሳባችሁን/ ስላጋራችሁን እናመሰግናለን። አሁን ለማሻሻል ምን መሥራት እንዳለብን ሁላችንም አውቀናል። እናንተ የሰጣችኋቸውን ምሳሌዎች በምንመለከትበት ጊዜ (እባካችሁ ጥቀሷቸው)፤ እነዚህ  ወሳኝ ተግዳሮቶች ነበሩ። ይህን መስማት በጣም የሚያስደንቅ ነበር፤ ስለዚህ ለ      ደቂቃ ያህል አጭር እረፍት እናድርግ። ከእረፍት ስንመለስ ምንም ያህል ድሀ ቢሆኑም አባቶች ለቤተሰባቸው እና ለልጆቻቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ እነግራችኋለሁ። በማህበረሰባችን ውስጥ ኩራት የሚሰማቸው እና አሳቢ አባቶችን መፍጠር ስለምንችልበት መንገድ ሀሳቦችን ለማግኘት በጋራ እንሰራለን።

ልጆችን በመንከባከብ ውስጥ የአባቶች ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ማቅረብከእረፍቱ በኋላ አባቶች በልጆቻቸው ህይወት ውስጥ መሳተፋቸው አዎንታዊ እና አስፈላጊ ስለመሆኑ ገለጻ አድርጉ። አባቶች ለልጆቻቸው ዕድገት አስፈላጊ ስለመሆናቸው እና ወጣት ወንዶች እና ሴቶች የአባታቸውን አመራር የሚናፍቁ ስለመሆኑ ከርዕስ ሀ ውስጥ የተወሰኑ ምሳሌዎችን ልትወስዱ ትችላላችሁ።

የአባት ተሳትፎን ለመደገፍ የሚረዱ ሀሳቦችን እንዲያቀርቡ ታዳሚዎቹን ማበረታታት
ቡድኑን ማዳመጥ መነሳሳትን የፈጠረባችሁ ከሆነ መሥራት ስለሚቻሉ ሥራዎች  የራሳችሁ የተወሰኑ ሀሳቦች ሊኖሯችሁ ይችላል። ነገር ግን ዝም ብላችሁ ብትቆዩ እና ታዳሚዎቹን የራሳቸውን መፍትሄዎች እንዲያገኙ ብታበረታቱ የተሻለ ነው። ምንአልባት መጨረሻ ላይ እናንተ እያሰባችኋቸው ካላችኋቸው ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ሀሳቦችን ሊያቀርቡ ይችላሉ፤ ነገር ግን በራሳቸው መንገድ ስላገኟቸው ይበልጥ የራሳቸው እንደሆኑ ይሰማቸዋል።

አሁን ሀሳቦችን እና ሥራዎችን እንዲያቀርቡ ማበረታታት መጀመር ትችላላችሁ። ሦስት ምሳሌዎች እንደሚከተለው የቀረቡ ቢሆንም የራሳችሁን እና ከታዳሚዎች የሚቀርቡ ሀሳቦችን ተከተሉ (ሌሎች ጥያቄዎችንም መጠየቅ ትችላላችሁ)፡-


“እንኳን ተመልሳችሁ በደህና መጣችሁ! እረፍት ከመውሰዳችን በፊት አባቶች በሦስት ጉዳዮች ላይ ተግዳሮት እንደሚያጋጥማቸው ተመልክተናል። አሁን ደግሞ ተጋግዘን ሀሳቦችን እናምጣ! በማህበረሰባችን ውስጥ መሥራት የምንችለው እንዴት ነው? በቤተሰባቸው ውስጥ እንዲሳተፉ እና ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ አባቶችን ማበረታታት እና በማንነታቸው እንዲኮሩ ማድረግ አለብን። በሦስት ቡድኖች ተከፋፍላችሁ ሦስት ጥያቄዎች ላይ እንድትሰሩ እጠይቃችኋለሁ (እባካችሁ ቡድኖቹን ግለጹ)። እባካችሁ ለ20 ደቂቃ አብራችሁ ስሩ። ከዚያ በኋላ ሀሳቦቻችሁን እና አስተያየቶቻችሁን አዳምጣለሁ”፡-

ቡድን 1፡- ለአባቶች የማህበረሰብ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖችን መፍጠር እንችላለን?
ለምሳሌ አባቶች ከልጆቻቸው እና ከባለቤታቸው ጋር የተያያዙ ችግሮቻቸውን ማጋራት የሚችሉበት ልምድ ያላቸው ወንዶችን የያዘ አነስተኛ ቡድን። አባቶች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ ሊማሩ እና ግጭቶችን ፈትተው ወደ ቤተሰባቸው ለመመለስ የሚያስችል ድጋፍ እና ምክር ሊያገኙ ይችላሉ። ይህም ፍቺዎችን፣ ንጥረ ነገሮችን ያለአግባብ መጠቀምን እና የአባቶች መገለልን ሊከላከል ይችላል። ለአባቶች ድጋፍ ሰጪ ቡድኖችን ከመፍጠር ጋር የተያያዙ ሌሎች ሀሳቦች አሏችሁ?

ቡድን 2፡– በማህበረሰቡ ውስጥ ለአባቶች እና ለልጆቻቸው እንቅስቃሴዎችን ማዘጋጀት እንችላለን?
እነዚህ እንቅስቃሴዎች የማህበረሰብ የእግር ኳስ ጨዋታዎች፣ ስፖርቶች፣ የጨዋታ እንቅስቃሴዎች፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚከበሩ የአባቶች ቀኖች ሊሆኑ ይችላሉ። አባቶች እና ልጆች አብረው እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ሊደሰቱ እና ሊዝናኑ የሚችሉባቸው ሌሎች ሀሳቦች አሏችሁ?

ቡድን 3፡- በቅርቡ አባት ለሚሆኑ ወጣት ወንዶች የማህበረሰብ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖችን መፍጠር እንችላለን?
ወጣት ወንዶች የአባታቸውን አመራር የሚሹ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ከወላጆቻቸው ምክር መቀበል ይከብዳቸዋል። አባት ለሆኑ ወይም በቅርቡ አባት ለሚሆኑ ወጣት ወንዶች የስብሰባ ቡድን ማዘጋጀት እንችላለን? ምን አልባትም በአንድ ወይም ሁለት ልምድ ያላቸው አባቶች የሚመራ? ሌሎች ሀሳቦች አሏችሁ?

ቡድን 4፡- እናቶች እና አባቶች ከእንክብካቤ ጋር የተያያዙ ችግሮች ላይ የሚወያዩባቸው ቡድኖችን መፍጠር እንችላለን?
ብዙ ሴቶች የልጃቸው አባት ጥሏቸው በመሄዱ ወይም ልጆቹን በመንከባከብ ውስጥ ባለመሳተፉ ቅሬታ እና ጭንቀት ይሰማቸዋል። እናቶች እና አባቶችን እንዲወያዩ፣ እንዲታረቁ እና መልሰው እንዲስማሙ ልንጋብዛቸው እንችላለን? አንዳንድ ጊዜ በወላጆች መካከል መተማመንን መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልገው የአባትየው ተሳትፎ ላይ የተወሰኑ ለውጦችን ማድረግ ብቻ ነው። አንድ አባት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ካሉ ልጆቹ ጋር ውይይቶችን ሊያደርግ እና ችግሮቻቸውን ሊያዳምጥ እንዲሁም ከህጻን ልጆቹ ጋር ሊጫወት ይችላል። እናትየው እርጉዝ ከሆነችም የሀኪም ቤት ቀጠሮዎች ላይ ሊሳተፍ፣ ወዘተ ይችላል። ትንንሽ እርምጃዎችን መውሰድ እና በቀላል ተግባራት መጀመር አስፈላጊ ነው፡፡

ቡድኖቹ የሚያቀርቧቸውን ሀሳቦች እና አስተያየቶች ካዳመጣችሁ እና ከጻፋችሁ በኋላ ስብሰባውን እንደሚከተለው መዝጋት ትችላላችሁ፡- “እነዚህን ድንቅ ሀሳቦች ስለሰጣችሁን እናመሰግናለን! እነዚህን ስራዎች እንዴት እንደምንጀምራቸው ለማቀድ ቀጣይ ስብሰባ (ቀን፣ ቦታ፣ ሠዓት) እንድናደርግ ሀሳብ አቀርባለሁ። በስብሰባው ላይ ለመገኘት እና ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ  ማናቸውንም በማስጀመር ለማገዝ ፈቃደኛ ነኝ። ይህ ለአባቶች እና ለልጆች በጣም የሚጠቅማቸው እንደሚሆን እና በማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን ትስስር እንደሚያጠናክረው እርግጠኛ ነኝ!!”

አባቶች ከማህበረሰቡ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማመቻቸት የሚወሰዱ ቀጣይ እርምጃዎች – የእናንተ ሀሳቦች

በሂደቱ ላይ ሀሳብ ከተለዋወጣችሁ እና በውጤቶቹ ላይ ከተወያያችሁ በኋላ ተጨማሪ ስብሰባዎችን ማቀድ እና ሌሎች ቡድኖችን መጋበዝ ትችላላችሁ። ለምሳሌ የአባትን ተሳትፎ እንዲገነዘቡ እና በዚያ ላይ እንዲወያዩ በአካባቢው ያሉ እናቶችን መጋበዝ። አባቶችን እና ወጣት ወንድ ልጆቻቸውንም በንቃት ተሳትፎ የሚያደርግ አባት ስለመሆን እንዲወያዩ ልትጋብዙ ትችላላችሁ። በማህበረሰቡ ውስጥ ካሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቡድኖች እና ግለሰቦች ጋር በጋራ በመሆን አባቶችን በተመለከተ አብራችሁ መሥራት ትችላላችሁ።

እንዴት ነው የምትቀጥሉት የሚለው የሚወሰነው የራሳችሁን ሀሳቦች እና ሥራ በምትሰሩበት ማህበረሰብ ውስጥ ያሉትን ሁኔታዎች መሠረት በማድረግ ነው።

በአባትነት ዙሪያ የማህበረሰብ ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት የሚረዳ ደረጃ በደረጃ የተቀመጠ ዝርዝር
  • የምስራቅ አፍሪካ አባቶች ልጆቻቸውን ከመንከባከብ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች አስቤባቸዋለሁ።
  • አባቶች ድሀ እና ሥራ አጥ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳን የአባት ተሳትፎ ስለሚያመጣቸው በርካታ አዎንታዊ ውጤቶች ገለጻ ማድረግ እችላለሁ።
  • በአባት እና በልጅ መካከል በየጊዜው የሚደረግ መስተጋብር፣ የአባት መገኘት መቻል እና የአባት ኃላፊነት የሚሉትን ሀሳቦች በዕለት ተዕለት ቃላት መግለጽ እና ምሳሌዎችን መስጠት እችላለሁ።
  • በማህበረሰቡ ውስጥ ላሉ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት አሳውቄአለሁ እንዲሁም ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጌአለሁ።
  • አንድን የማህበረሰብ ቡድን የመጀመሪያ ስብሰባ ለማድረግ ጠርቼአለሁ።
  • አባቶች ለቤተሰብ እና ለልጆች ደህንነት አስፈላጊ እንደሆኑ የሚያስረዳ የግል ምሳሌ አዘጋጅቼአለሁ።
  • የአባት ተሳትፎ ስለሚያስገኛቸው ዋና ዋና ጥቅሞች ገለጻ አድርጌአለሁ።
  • ታዳሚ በሆነው ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ውስንነቶችን መገንዘብ እና ተስፋ መፍጠር ስለሚቻልበት መንገድ ተወያይቼአለሁ።
  • የመጀመሪያው ስብሰባ ስላስገኛቸው ውጤቶች ተወያይቼአለሁ።
  • የአባቶችን ተሳትፎ እንዲደግፍ ማህበረሰቡን ለማበረታታት ተጨማሪ እንቅስቃሴዎችን አቅጄአለሁ።
  • ለአባቶች አንዳንድ ስብሰባዎችን ሳከናውን አባቶች እና እናቶችን የያዘ ቅልቅል ቡድን መጋበዝ የሚለውን አስቤበታለሁ።