ክፍለ ጊዜ 13/21

ገጽ 3/5 ርዕስ ሀ፡- ልጆቻቸው የአደራ ቤተሰብ እንክብካቤ እንዲያገኙ የተመደቡ ወላጆች ላይ የተለመደው ነገር ምንድን ነው?

ልጆቻቸው የአደራ ቤተሰብ እንክብካቤ እንዲያገኙ የተመደቡ ወላጆች ላይ የተለመደው ነገር ምንድን ነው?

እባካችሁ የሚከተሉትን ልጆቻቸው የአደራ ቤተሰብ እንክብካቤ ላይ ያሉ ወላጆች ባህሪያት ተመልከቱ እና የእናንተ የአደራ ቤተሰብ ልጅ ወላጆች የሚያሳዩአቸው የተለመዱ ባህሪያት የትኞቹ እንደሆኑ ተወያዩ፡-
1. ወላጅነታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ሁኔታዎች ያስገደዷቸው መደበኛ ወላጆች
ጥሩ እንክብካቤ ሰጪዎች ይሆኑ የነበሩ ወላጆች ልጃቸው የአደራ ቤተሰብ እንክብካቤ ውስጥ ቢሆን ይሻለዋል ብለው እንዲወስኑ በውጫዊ ሁኔታዎች የተነሳ ሊገደዱ ይችላሉ።
ለዚህም ምክንያቶቹ አብዛኛውን ጊዜ የሚከተሉት ናቸው፡-

ሀ. ከጋብቻ ውጭ በማርገዛቸው የተነሳ ከቤተሰባቸው የተባረሩ ወይም የወላጅነት ክህሎታቸውን ለመጠቀም ዕድሜአቸው ያልደረሰ ያለአባት ልጃቸውን የሚያሳድጉ እናቶች።

ለ. በአሰቃቂ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፉ ወለጆች፡- ለምሳሌ ተገደው የተደፈሩ እናቶች፣ እንደ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ጎርፍ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ተጠቂዎች፣ የኢኮኖሚ ቀውስ ወይም ሥራቸውን ማጣት፣ በከባድ አካላዊ ህመም የተነሳ የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ወላጆች ወይም የአንደኛው ወይም ሁለቱም ወላጆች መሞት።

ሐ. ህጻኑ ከባድ አካላዊ ችግር ኖሮበት የተወለደባቸው እና/ወይም ጊዜው ሳይደርስ ወይም በጣም አነስተኛ ክብደት ኖሮት እና ብዙ የጤና ችግሮች ኖረውት የተወለደባቸው ቤተሰቦች።

መ. እናትየው ከህጻን ልጇ ጋር ምንም አካላዊ ንክኪ ያላደረገችባቸው ቤተሰቦች (ለምሳሌ ህጻኑ የማዋለጃ ክፍሉ ውስጥ ከእናቱ ጋር ተለያይቶ ወይም ከተወለደ በኋላ ለረጅም ጊዜ የሙቀት ክፍል ውስጥ ቆይቶ ሊሆን ይችላል። ከወሊድ በኋላ በአካል መለያየት ካለ ማንኛውም ወላጅ ከህጻኑ ጋር የቅርበት ስሜት እንዲሰማው ለማድረግ ይቸገራል እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ የህጻኑን መገፋት ያስከትላል።

ስለ ወላጆቹ ያሏችሁ አስተያየቶች፡-
የአደራ ቤተሰብ ልጃችሁን የተፈጥሮ ወላጆች ይህ መግለጫ በጥቅሉ ይገልጻቸዋል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አዎን፡-….. ወይስ አይ፡-…..

በጥቅሉ ስንመለከተው ወላጅነታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ከሁኔታዎች የተነሳ ከተገደዱ ወላጆች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ማለት እነዚህ ወላጆች የወላጅነት ክህሎቶች አሏቸው እንዲሁም እንድታከብሯቸው እና ያሉበትን ሁኔታ እንድትገነዘቡላቸው ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው።
እነዚህ ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ ልጃቸው ለምን የአደራ ቤተሰብ እንክብካቤ ውስጥ መሆን እንዳለበት የሚገነዘቡ ከመሆኑም በላይ እናንተ ልትደግፏቸው እንደምትችሉት ሁሉ እነሱም ሊደግፏችሁ ይችላሉ።

2. የተጎዱ ወላጆች
ሀ. አንደኛው ወይም ሁለቱም ወላጆች የራሳቸውን ህይወት ለመምራት በጽኑ ሁኔታ የማይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ እንዲሁም ከዚህ በተጨማሪ (ምንም እንኳን ልጃቸውን ሊወዱት ቢችሉም) ከሞላ ጎደል አስተማማኝ እና ተጨባጭ በሆነ መልኩ ልጃቸውን ለመንከባከብ የማይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ያሉትን ቤተሰቦች በተመለከተ በእናንተ እንክብካቤ ስር ያለው ህጻን በጣም ህጻን እያለ እንክብካቤን ተነፍጎ የነበረ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ከእናንተ ጋር ከመቀራረብ ጋር በተያያዘ ከባድ ችግር ይኖርበታል (ይህን ርዕሰ ጉዳይ በክፍለ ጊዜ 4 አና 5 ውስጥ ይበልጥ ማጥናት ትችላላችሁ)።

ለ. አባትየው በተደጋጋሚ በብዙ የእንጀራ አባቶች የሚተካባቸው ቤተሰቦች (ይህ እናትየው ከአዋቂዎች ጋር እንዲሁም ከህጻናት ጋር ዘላቂ ግንኙነቶችን ለመመስረት የማትችል መሆኑን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል)። አባትየው በሚስትየው እና በልጆቹ ላይ ኃይል የሚጠቀምባቸው ቤተሰቦች። ኃላፊነት የሚሰማው ወላጅ መሆን የሚችል አባት የሌለባቸው ቤተሰቦች።

ሐ. ራሷ ልጅ እያለች በጣም የተነፈገች እና ምንም ዓይነት የወላጅ አመራር ያላገኘች እናት (ወይም አባት) ያላቸው ቤተሰቦች። ከስሜት አንጻር እንዲህ ያሉት ወላጆች በጣም ያልበሰሉ ሊሆኑ እና ከወላጅ ይልቅ የልጅ ባህሪ ሊታይባቸው ይችላል፡- ስሜታዊ መሆን፣ ቀጠሮዎችን ማስታወስ ያለመቻል፣ ስምምነት የተደረገበትን ነገር ማቀድ እና ተግባራዊ ማድረግ ያለመቻል፣ በማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ ምን ዓይነት ባህሪ ማሳየት እንዳለባቸው ያለማወቅ።

መ. የአእምሮ ችግር ያለበት የመጀመሪያ ደረጃ እንክብካቤ ሰጪ (ህጻኑ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ሦስት ዓመት እስከሚሞላው ድረስ) ያላቸው ቤተሰቦች፡- ስኪዞፍሬኒያ (Schizophrenia)፣ ባይፖላር ዲሶርደር (Bipolar disorder)፣ ቦርደርላይን ፐርሰናሊቲ ዲስተርባንስ (Borderline Personality Disturbance)፣ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ድባቴ (post partum depression) ወይም በርዝ ሳይኮሲስ (birth psychosis)። በአጭሩ እናትየው ወይም አባትየው የአእምሮ በሽታ ያለባቸው ሲሆኑ እና በዚህም የተነሳ ህጻን ልጃቸውን መንከባከብ ሳይችሉ ሲቀሩ ማለት ነው።

ሠ. ከፍተኛ አግባብ ያልሆነ የአልኮል ወይም የዕጽ አጠቃቀም ችግር ያለበት እና/ወይም በወንጀል ድርጊቶች ውስጥ የተሳተፈ አንድ ወይም ሁለት ወላጅ ያለባቸው ቤተሰቦች።

ከተወለዱ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በጣም ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው የህጻናት ማሳደጊያዎች ውስጥ ያደጉ እና በዘፈቀደ ካገኟቸው እንክብካቤ ሰጪዎች በጣም አነስተኛ እንክብካቤ ያገኙ ወላጆች። አንዳንድ የህጻናት ማሳደጊያዎች የሠራተኛ እጥረት ያለባቸው በመሆኑ ህጻናቱን አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማሳደግ ይቸገራሉ እንዲሁም እንክብካቤ ሰጪዎች ከህጻናቱ ጋር ማህበራዊ እና የስሜት ግንኙነቶችን በመመስረት ውስጥ ላይሳተፉ ይችላሉ።

ስለ ወላጆቹ ያሏችሁ አስተያየቶች፡-
የአደራ ቤተሰብ ልጃችሁን ወላጆች (ወይም የመጀመሪያ እንክብካቤ ሰጪዎች) ይህ መግለጫ በጥቅሉ ይገልጻቸዋል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አዎን፡-….. ወይስ አይ፡-…..

በጥቅሉ ስንመለከተው ከተጎዱ ወላጆች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ለአደራ ቤተሰብ ወላጆች በጣም ከባድ ነው። ከላይ የተገለጹት ባህሪያት በእንክብካቤ ላይ ያለውን ህጻን ወላጆች ይበልጥ የሚገልጹ በሆነ ቁጥር ለአደራ ቤተሰብ ወላጆቹ ተቀናጅቶ መሥራት ይበልጥ ከባድ ይሆናል። የተጎዱ ወላጆች ልጆቻቸውን ከማሳደግ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከባለስልጣን አካላት፣ ከራሳቸው ቤተሰቦች እና ከአደራ ቤተሰቡ ጋር ያሏቸውን ግንኙነቶች ጨምሮ ከሚያጋጥሟቸው ማናቸውም ማህበራዊ ግንኙነቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የማህበራዊ ግንኙነት ችግሮች አሉባቸው።