ክፍለ ጊዜ 21/21
ገጽ፡- 2/6: ርዕስ ሀ፡- ከትውልድ ቤተሰብ ጋር መልሶ መቀላቀልን የተመለከተ መግቢያርዕስ ሀ፡- ከትውልድ ቤተሰብ ጋር መልሶ መቀላቀልን የተመለከተ መግቢያ
ከትውልድ ቤተሰብ ጋር መልሶ መቀላቀል እና የቤተሰብ መልሶ መዋሀድ ማለት ምን ማለት ነው?
ይህ የመስሪያ ቤቶች መመሪያ ለሁሉም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና መንግስታት የመልሶ መቀላቀልን ትርጓሜ እንደሚከተለው ያስቀምጣል፡-
“ጥበቃ እና እንክብካቤ ለማግኘት እና በሁሉም የህይወት ዘርፎች ውስጥ የእኔነት ስሜት እና ዓላማ እንዳለው እንዲሰማው/ት አንድ/ዲት ከቤተሰቡ/ቧ ጋር የተለያየ/ች ህጻን ወደ ቤተሰቡ/ቧ እና ማህበረሰቡ/ቧ (አብዛኛውን ጊዜ የትውልድ) ቋሚ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቅ መልኩ የሚመለስበት/የምትመለስበት ሂደት ነው።”
በዚህ ክፍለ ጊዜ ውስጥ የቤተሰብ መልሶ መገናኘትን በመገንዘብ እና ከወላጆች እና ከዘመዶች ጋር በማቀድ ላይ እናተኩራለን። የሚከተሉት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መልሶ መቀላቀል የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶች ናቸው፡-
- አንድ ህጻን ወይም ወጣት ከአንድ/ዲት የኤስ ኦ ኤስ አሳዳጊ ጋር በአካባቢው ያለ የአደራ እንክብካቤ ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል (ይህ ርዕስ ክፍለ ጊዜ 20 ውስጥ ተሸፍኗል)
- አንድ ወጣት ከእንክብካቤ ወጥቶ በማህበረሰቡ ውስጥ እራሱን ችሎ መኖር ሊጀምር ይችላል (ይህ ርዕስ ክፍለ ጊዜ 14 እና 15 ውስጥ ተሸፍኗል)
- አንድ ህጻን በአካባቢው ባለ ቤተሰብ ሕጋዊ በሆነ መልኩ በጉዲፈቻ ሊወሰድ ይችላል። ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ይህን አሰራር አይጠቀምም
ህጻናትን እና ወጣቶችን ከትውልድ ቤተሰባቸው ጋር መልሶ መቀላቀል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?
አዲሱ የኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ህጻናትን ከህብረተሰቡ ጋር መልሶ የመቀላቀል እ.ኤ.አ. የ2030 ስትራቴጂ ህጻናትን ያማከለ ዘዴን ተግባራዊ ያደርጋል። ስትራቴጂው በመጀመሪያ ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ህጻኑ ያለውን የባህል ማንነት፣ የቤተሰብ እና የማህበራዊ ትስስር መብት ማረጋገጥ ነው።
ከዚህ ቀደም አስተማማኝ በሆኑት የኤስ ኦ ኤስ መንደሮች ውስጥ የነበሩ ህጻናት ከማህበረሰብ ከሚመነጩ አደጋዎች እና ከህጻናት የተተው መሆን (child abandonment) የተጠበቁ ነበሩ። ዋነኛ የስሜት ቁርኝታቸው ከኤስኦኤስ አሳዳጊአቸው እና በቤቱ ውስጥ ካሉ ሌሎች ህጻናት ጋር ነበር። እነዚህ ውጤቶች በጣም ስኬታማ በመሆናቸው አሳዳጊዎች እና መምህራን ሊመሰገኑ ይገባል።
ታዲያ ከትውልድ ቤተሰብ ጋር መልሶ መቀላቀል ለምን አስፈለገ? ምንም እንኳን የኤስ ኦ ኤስ መንደር የሚለው ሞዴል ለተወሰኑ ህጻናት የህጻናት ዕድገትን ያሻሻለ ቢሆንም የአካባቢ ማህበረሰቦች ያላቸውን ህጻናትን በሙሉ የመንከባከብ ችሎታ አላጠናከረም። በተጨማሪም የኤስ ኦ ኤስ አሳዳጊዎች እና ህጻናት አብዛኛውን ጊዜ ከማህበረሰባቸው ይነጠሉ ነበር። አነስተኛ ዕድሜ ላይ እያሉ ከእንክብካቤ ለሚወጡ ልጆች ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነ ቦታ ካደጉ በኋላ ከዘመዶቻቸው ጋር መልሰው መገናኘት እና በማህበረሰቡ ውስጥ መኖር ፈታኝ ነበር።
የኤስ ኦ ኤስ ህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሳህለማርያም አበበ አዲሱን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሚከተለው ይገልጹታል፡- “በአየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎች ጫና ፈጣሪ ጉዳዮች የተነሳ ስጋት የተጋረጠባቸው ህጻናት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ለተወሰኑ የተነጠሉ ህጻናት ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ መፍፍሄዎችን ከመፈለግ ይልቅ (ይህ ማለት እያንዳንዱ ህጻን በነፍስ ወከፍ የሚኖረው የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ ይሆናል ማለት ቢሆንም እንኳን) የህብረተሰባችንን አቅም በአጠቃላይ ማጎልበት አለብን”። ይህን ለማድረግ ሁሉም ሰው ከባድ የሆነ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል፡- “በአሁኑ ወቅት በህብረተሰቡ ውስጥ ለስጋት ተጋላጭ የሆኑ ወላጆች የኤስ ኦ ኤስ መንደር ለልጃቸው ሁነኛው መፍትሄ እንደሆነ ያስባሉ። የኤስ ኦ ኤስ እናቶች ከኤስ ኦ ኤስ መንደር ለመውጣት ይፈራሉ፤ የአካባቢውን ባህል እና ቋንቋ ለመልመድም ይገደዳሉ። ህጻናት እና ወጣቶች ከእናታቸው ጋር ጥልቅ የሆነ ቁርኝት አላቸው። ከእናታቸው ጋር ለመለያየት እና ከትውልድ ቤተሰባቸው ጋር ለመኖር መፍራታቸው ተፈጥሮአዊ ነው”።
የ15 ደቂቃ የቡድን ውይይት፡-
- ከትውልድ ቤተሰብ ጋር መልሶ ስለመቀላቀል ስናስብ መጀመሪያ አእምሮአችን ላይ የሚመጡት ሀሳቦች ምንድን ናቸው?
- በሂደቱ ውስጥ ምን ምን ጥቅሞች እና ተግዳሮቶች ይኖራሉ ብለን እንጠብቃለን?
- እባካችሁ የሥራ አመራር ድጋፍ ልናገኝባቸው ያስፈልጋል የምትሏቸው ሦስት ነገሮች ላይ ተስማሙ።
ህጻንን ያማከለ ከቤተሰብ ጋር መልሶ የማዋሀድ ዘዴ ምንድን ነው?
ህጻንን ያማከለ ዘዴ ማለት ዝግጅቶችን ከማድረግ አንስቶ ከዘመዶች ጋር እስከመኖር ድረስ በሁሉም ምዕራፎች ውስጥ ህጻናት እና ወጣቶች ድምጻቸው መሰማት አለበት ማለት ነው። በሁሉም ዕቅዶች እና ውሳኔዎች ውስጥ የእውነት ተጽዕኖ ሊኖራቸው እና ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል። በተለይም ደግሞ በኤስ ኦ ኤስ መንደሩ ውስጥ ከኤስ ኦ ኤስ እናታቸው እና ከጓደኞቻቸው ጋር ያሏቸውን የስሜት ቁርኝቶች ከዘመዶቻቸው እና ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሚፈጥሩት አስተማማኝ የሆኑ አዳዲስ ቁርኝቶች በመተካቱ ሂደት ውስጥ ድምጽ ሊኖራቸው ይገባል። ህጻናት በእንክብካቤ ውስጥ እያሉ ዘመዶቻቸውን አፈላልጎ ለማግኘት እና ለማነጋገር ጥረቶች መደረግ አለባቸው።
ከዚህ በፊት የኤስ ኦ ኤስ መንደር ውስጥ የሚኖር ህጻን የነበረው የ34 ዓመቱ አስቻለው አሁን የተሳካለት ነጋዴ ነው። ድሮ ኤስ ኦ ኤስ መንደር ውስጥ እያለ ዘመዶቹ እንዳይጠይቁት ይከለክል የነበረው አሰራር የፈጠረበትን ስቃይ አሁንም ያስታውሰዋል። በኋላ ላይ ደግሞ ቤተሰቦቹ እንዲጠይቁት የሚፈቀድላቸው የነበረው በወር ለአንድ ሠዓት ብቻ ነበር። ትዕግስት ደግሞ (አሁን ዕድሜዋ 25 ዓመት ነው) በዕድሜ አነስ ትል የነበረ ሲሆን በኤስ ኦ ኤስ መንደር ውስጥ በነበረችበት ወቅት ዘመዶቿን ሁል ጊዜም ታገኛቸው ስለነበር ደስተኛ ነበረች።
ስኬታማ የሆነ የቤተሰብ መልሶ መገናኘት አራት መሪ መርሆዎች
ህጻናት ከእንክብካቤ ሰጪዎቻቸው ጋር ያሏቸው ግንኙነቶች እና ቁርኝቶች እጅግ ወሳኝ መገለጫዎቻቸው በአፍሪካ በተከናወኑ እና በዓለም አቀፍ ጥናቶች ውስጥ በአጭሩ ተቀምጠዋል። እነዚህ መገለጫዎቻቸው በህጻንነት ወቅት ይበልጥ በተሟሉ ቁጥር ህጻኑ አዋቂ በሚሆንበት ወቅት (በትምህርት፣ በዕለት ተዕለት ክህሎቶች እና ማህበራዊ ትስስሮችን በመመስረት ረገድ) ይበልጥ ስኬታማ የመሆን ዕድሉ ይጨምራል። አራቱ መርሆዎች በኤስ ኦ ኤስ መንደር ውስጥ ከመኖር ወደ ዘመዶች ወደ መመለስ ከሚደረገው ሽግግር ጋር በተያያዘ ለምንሰራው ስራ እንደ መመሪያ ሊገለግሉ ይችላሉ፡-
- ከአንድ እንክብካቤ ሰጪ ጋር ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ቁርኝት መፍጠር እና ቁርኝቱ ወደ ሌላ ሰው እንዲሸጋገር ማገዝ።
- በአዲሶቹ እኩዮች ዘንድ ተቀባይነት ያለው አባል መሆን።
- ህጻኑ እና እንክብካቤ ሰጪዎቹ ንቁ እና በቂ መረጃ ያላቸው ተሳታፊዎች መሆን አለባቸው።
- ህጻኑ በተቆራኛቸው ሰዎች እና በህይወቱ ውስጥ ውሳኔዎችን በሚወስኑት ሰዎች (ሥራ አስኪያጆች፣ የኤስ ኦ ኤስ እናቶች፣ ወላጆች እና ዘመዶች፣ መምህራን እና የማህበረሰብ አባላት) መካከል ስምምነት መኖር አለበት።
የ20 ደቂቃ የቡድን ውይይት፡–
- እባካችሁ ተወያዩ፡- ከቤተሰብ ጋር መልሶ መቀላቀልን በምናቅድበት ወቅት እነዚህን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?