ክፍለ ጊዜ 10/19

ገጽ 3/7 ርዕስ ሀ፡- ህጻናት የቤተሰብ መልክ በሌለው እንክብካቤ ውስጥ በሚመደቡበት ወቅት አስተማማኝ መሠረት የሚሆን ግሩፕ ያለመኖር

ርዕስ ሀ፡- ህጻናት የቤተሰብ መልክ በሌለው እንክብካቤ ውስጥ በሚመደቡበት ወቅት አስተማማኝ መሠረት የሚሆን ግሩፕ ያለመኖር

ዛሬ ትኩረት የምናደርግበት ነገር ለምን አስፈላጊ ነው?

አንዳንድ ጊዜ በአደራ ቤተሰብ እንክብካቤ ውስጥ ያሉ ህጻናት እና ታዳጊዎች ከወላጆቻቸው ጋር መለያየትን ብቻ ያሳለፉ ላይሆኑ ይችላሉ። ምን አልባት ከእናንተ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ከዚያ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችን አጥተው እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ተለያይተው ሊሆን ይችላል። ምን አልባት በርካታ የአደራ ቤተሰቦች ውስጥ የተመደቡ፣ ከዘመዶች ጋር ወይም እንክብካቤ ሰጪዎች በተደጋጋሚ ይለዋወጡባቸው የነበሩ የህጻናት ማሳደጊያዎች ውስጥ የኖሩ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም እንደ ፍቺ፣ የልጅ አሳዳጊ የመሆን ክርክር፣ ወዘተ የመሳሰሉ በርካታ ግጭቶች በወላጆቻቸው መካከል ሲፈጠሩ ያዩ ሊሆኑ ይችላሉ።

ህጻናት አስተማማኝ እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የእንክብካቤ ሰጪ ግንኙነት ሲጎድላቸው መተማመን የጎደላቸው የአቀራረብ ባህሪዎችን በማዳበር ምላሽ ይሰጣሉ (በክፍለ ጊዜ 9 እንደተማራችሁት፡- የመሸሽ፣ የመጠራጠር እና የተዘበራረቀ)። የአደራ ቤተሰብ ውስጥ በሚገቡበት ወቅት በዕለት ተዕለት መስተጋብሮች ውጥ የኃይለኝነት፣ የመደንዘዝ ወይም ሳይለዩ ሰውን በጣም የመቅረብ ባህሪዎችን ሊያሳዩ ይችላሉ። ምን ማለት እና ማድረግ እንዳለባቸው እና በቤተሰቡ ውስጥ ላሉ ሌሎች ሰዎች ምን ዓይነት ባህሪ ማሳየት እንዳለባቸው ለመገንዘብ ሊቸገሩ ይችላሉ። ይህ ለሁሉም የቤተሰቡ አባላት እንዲሁም በቤተሰቡ ውስጥ ያሉትን ማህበራዊ ደንቦች መረዳት እና ተግባራዊ ማድረግ ሲያቅተው እንደማይፈለግ ሊሰማው ስለሚችል ለህጻኑ በጣም የሚረብሽ ተሞክሮ ሊሆን ይችላል።

ስለሆነም እነዚህን ችግሮች በመቋቋም ማህበራዊ ግንኙነቶችን በአግባቡ ለማከናወን እና ህጻኑ ቤተሰብነት እና ቅርርብ እንዲሰማው ለማድረግ የሚያስችሉ መንገዶችን ማግኘት ብዙ ማሰብ፣ መወያየት እና ማቀድ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ህጻኑ ቀስ በቀስ የዕለት ተዕለት እንክብካቤዎችን እንዴት ማስኬድ እንዳለበት እንዲለምድ ማድረግ ያስፈልጋል። አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ ድርሻ እና መታለፍ ከሌለባቸው መስመሮች ጋር በተያያዘ ያሉት አሠራሮች የራሱን የቤተሰቡን ልጆች ጨምሮ ለሁሉም የቤተሰቡ አባላት የሚሰሩ እስከሚሆኑ ድረስ ከፍተኛ እና ትዕግስት የተሞላበት ጥረት ማድረግን ይጠይቃል።

ከከባድ የጀርባ ታሪክ የመጡ ህጻናትም እንኳን ይህን ሊማሩ ይችላሉ። ከአደራ ቤተሰብ ወላጆች እና ባለሞያዎች ትዕግስት የተሞላበት ድጋፍ ካገኙ ጠቅላይ ሚኒሰትርም ጭምር ሊሆኑ ይችላሉ።

በእንክብካቤ ላይ ላሉ ህጻናት ተግዳሮት የሚሆንባቸው ምንድን ነው፤ ለእነሱ እገዛ ለማድረግ በሚሞከርበት ወቅት ውጤት የሚያስገኘው ምንድን ነው?

በሕጻናት ማሳደጊያ ተቋማት እና በአደራ ቤተሰቦች ውስጥ ባደጉ ታዳጊዎች ላይ በተሠሩ ጥናቶች ውስጥ ለራስ ዝቅተኛ ግምት የመስጠት፣ የመገፋት እና የጎዳና ተዳዳሪነት በብዛት እንደሚሰማቸው ታዳጊዎቹ ገልጸዋል። በተጨማሪም እነሱ በጣም ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡት ነገር (የኔ የሚሉት ቦታ የማግኘት ፍላጎት) በሥርዓቱ ውስጥ ካሉት ሰዎች ውስጥ የሚያናግሯቸው በጣም ጥቂቱ ናቸው። የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ላይ በተሰራ ጥናት አብዛኞቻቸው በተቋማት ወይም በአደራ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። ይህ አሳዛኝ ክስተት ብዙ ጊዜ በአደራ ቤተሰቡ ውስጥ ህጻኑ የመካተት ስሜት እንዲሰማው የሚያደርጉ እና ማህበራዊ ችሎታዎቹን የሚገነቡ ሥራዎችን በመሥራት ለመከላከል የሚቻል ነው።

የቀድሞ የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር አንከር ጆርገንሰን ወላጆቻቸው የሞቱት ዕድሜያቸው አምስት ዓመት እያለ ነበር። ለፌርስታርት (Fairstart) በሰጡት ምክረ-ሀሳብ በፖለቲካ ውስጥ ስኬታማ ሊሆኑ የቻሉት የአደራ ቤተሰብ እናታቸው ከሆኑት ከአክስታቸው ባገኙት እንክብካቤ የተነሳ እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም በህይወታቸው ውስጥ በኋላ ላይ ያደጉበት የህጻናት ማሳደጊያ ጠንካራ ማህበራዊ ገጽታ ያለው ነበር። ይህም ማህበራዊ ኃላፊነት የመውሰድ እና በሞያቸው ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልገውን ድፍረት የማዳበር ጠንካራ ፍላጎትን ፈጥሮባቸዋል።

በአደራ ቤተሰብ እንክብካቤ ሥርዓቱ ውስጥ አድገው በህይወት ውስጥ ስኬታማ የሆኑ አዋቂዎች ሁሉም ስለ የልጅነት እንክብካቤ ሰጪዎቻቸው የሚገልጿቸው አራት ባህሪያት አሉ፡-

  • አንድ ወይም ሁለት እንክብካቤ ሰጪዎች በህይወታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ በጣም እንዲቀርቧቸው ፈቅደውላቸዋል። እነዚህ ግለሰቦች ቻይ ነበሩ እንዲሁም ቀስ በቀስ እንዲያድጉ ጊዜ ሰጥተዋቸዋል።
  • ሁሉም የራሳቸው የግል ጊዜ እና ቦታ ተሰጥቷቸዋል።
  • ከተፈጥሮ ቤተሰባቸው ያልተማሯቸውን ማህበራዊ ክህሎቶች የተማሩበት የጋራ መኖሪያ (የአደራ ቤተሰብ ወይም ተቋም) ውስጥ ኖረዋል።
  • የጋራ መኖሪያው ከአካባቢው ማህበራዊ መረብ ጋር ጥሩ ግንኙነቶች ነበሩት፤ ይህም ህጻኑ በማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት እንዳለው እንዲሰማው የሚያደርግ ነው።