ክፍለ ጊዜ 10/21
ገጽ 4/7 ለህጻኑ አስተማማኝ የሆነ የግል ጊዜ እና ቦታ መስጠት
ለህጻኑ አስተማማኝ የሆነ የግል ጊዜ እና ቦታ መስጠት
እንክብካቤ እንዲያገኝ የተመደበው ህጻን ወይም ታዳጊ ቀስ በቀስ የግል ጊዜ እና ቦታ እንዳለው እንዲሰማው እና በቤተሰቡ የራሱ ቤተሰብ እንደሆነ እንዲሰማው ልትረዱት የምትችሉት በምን መልኩ ነው?
እያንዳንዱ ህጻን የራሱ የሆነ ጊዜ እና ቦታ ሊኖረው ይገባል፡- ህጻኑ የራሱን ክፍል ወይም ስፍራ በማሳመር ውስጥ እንዲሳተፍ አድርጉ። ህጻኑ የመመገቢያ ጠረጴዛው ላይ የራሱ ወንበር ሊኖረው ይችላል። ምን አልባትም ህጻኑ ራሱ ወይም የአደራ ወላጆቹ ብቻ ሊከፍቱት የሚችሉት የሚቆለፍ የግል ሳጥን ሊኖረው ይችላል።
በተጨማሪም ህጻኑ የራሱ የሆነ የግል ጊዜ ሊኖረው ይገባል፡- በራሱ ክፍል ወይም ስፍራ ዘና የማለት መብት። የስሜት ወይም የባህሪ ችግሮች ላሉባቸው ህጻናት ቀላል እንቅስቃሴዎችም እንኳን (የተወሰኑ ሠዓታትን በት/ቤት እንደማሳለፍ ያሉ) እጅግ በጣም አድካሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ህጻኑ “አሁን ዘና በማለት፣ በመጫወት ወይም የቤት ሥራዬን በመሥራት የማሳልፈው የራሴ አንድ ሠዓት አለኝ” የሚለውን ነገር ማወቁ በራሱ የሚከላከላቸው በርካታ ችግሮች አሉ። በግል የሚያሳልፋቸው ጊዜዎችን መደበኛ በሆነ መልኩ መስጠት በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ጥሩ የሠዓት ግንዛቤ የሌላቸው ህጻናት ክፍላቸው ውስጥ በጣም ለአጭር ወይም በጣም ለረጅም ሠዓት የመቆየት ሁኔታ ይታይባቸዋል። ስለዚህ ህጻኑ መደበኛ በሆነ መልኩ አጭር እረፍቶችን እንዲወስድ መስማማት ድካምን እና መበሰጫጨቶችን ሊከላከል ይችላል።
ለጨቅላ ህጻናት እና ድክ ድክ ለሚሉ ህጻናት፡- የግል ጊዜ እና ቦታ የሚለው ነገር እንደ ቴዲ ቤር አሻንጉሊት፣ አሻንጉሊት፣ የተለየ ከነቴራ፣ ወዘተ ያለ ነገር ሊሆን ይችላል። በቤት ውስጥ የሚከተለውን ነገር ተወያይታችሁ ወስኑ፡- ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ዕቃው የህጻኑ መሆኑን እንደሚያከብሩ መግለጽ የሚችሉት እንዴት ነው?
ህጻኑ የራሱ የቤት እንሰሳ ያለው መሆኑ (አንድን ጥጃ፣ በግ፣ ዶሮዎችን ወይም ሌላ እንስሳ ለመንከባከብ ኃላፊነት እንደመውሰድ ያለ) ሰውን የመቅረብ ሁኔታን ሊያጠናከር ይችላል።
ብዙ ህጻናት ሰውን የመቅረብ ሂደትን የሚጀምሩት መጀመሪያ ከእንሰሳት ጋር በመቀራረብ ነው። ይህ ከሰው ጋር ከመቀራረብ ጋር ሲነጻጸር ውስብስብነቱ አነስተኛ ነው።
ህጻኑ/ድክ ድክ የሚለው ህጻን ስለራሱ ያለውን በማደግ ላይ ያለ ግንዛቤ መደገፍ፡- በመስታወት መጫወት ወይም ከሞባይል ስልክ ወይም ከካሴት ላይ የራሱን ድምጽ ለህጻኑ ማሰማት “እንዴ፣ እኔ ነኝ እኮ!” የሚለው ግንዘቤ እንዲኖረው ሊረዳ ይችላል።
በዕለት ተዕለት መስተጋብሮች ውስጥ የአደራ ቤተሰብ ወላጁ ህጻኑ የሚያደርገውን ነገር ቀለል አድርጎ በቃላት ሊገልጽ ይችላል (“አሁን ሸሚዝህን ለመቆለፍ እየሞከርክ ነው – በጣም ቀላል አይደለም ግን መሞከርህን አታቋርጥ)።
ስለእነዚህ ነገሮች ማውራት ህጻኑ ድርጊቶቹ በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ እና እንዴት ማዳመጥ፣ ማሰብ እና ምላሽ መስጠት እንዳለበት እንዲያውቅ የሚረዳ በጣም ጥሩ ዘዴ ነው።
ይህም ህጻኑ መስተጋብሮችን በሚያደርግበት ወቅት ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲገነዘብ ይረዳል። የሚታየው ባህሪ በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማወቅ በትንሽነት ዕድሜያቸው የሚያገኙት አመራር በጣም አነስተኛ በመሆኑ ብዙ የሚፈልጉትን ነገር አግኝተው ያላደጉ ህጻናት ለመገንዘብ የሚቸገሩት ነገር ነው።
ለህጻኑ ግብረ መልስ ስትሰጡት፡- በጣም ጥሩ እና አዎንታዊ ስለሆኑት መስተጋብሮች ብቻ አውሩ። ማናቸውንም አግባብ ያልሆኑ ምላሾች አትጥቀሱ። አዎንታዊ በሆኑት ድርጊቶች ላይ አተኩሩ።
በዕድሜ ተለቅ ላሉ ህጻናት እና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ለሚገኙ ህጻናት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች፡- በየቀኑ አስቀድሞ የተወሰነ ሠዓት ላይ (የዕንቅልፍ ሠዓት ጥሩ ነው) በዕለቱ ስለተፈጠሩት ነገሮች (ልጁ ወይም ወጣቱ ደስ ስለሚለው ማንኛውም ነገር) ከህጻኑ ወይም ከወጣቱ ጋር አጠር ያሉ ውይይቶችን አድርጉ። ይህን የግል ማስታወሻው ውስጥ እንዴት እንደሚጽፍ ከህጻኑ ጋር ተወያይታችሁ ወስኑ። ቀስ በቀስ ህጻኑ በራሱ አጠር አድርጎ እንዲጽፈው አድርጉ። ህጻኑ የማንበብ ችግር ካለበት አጠር ተደርጎ የሚጻፈው ነገር የህጻኑ ወይም የእናንተ ሞባይል ስልክ ላይ ሊቀዳ ይችላል። ይህ በዕለቱ የተፈጠሩትን ነገሮች በሙሉ ለማብላላት እና ህጻኑን ምን እንደሚያስብ እና ምን እንደሚሰማው እንዲያሰላስል ለማስተማር የሚጠቅም ጥሩ እንቅስቃሴ ነው። በተጨማሪም ይህ እንቅስቃሴ የማስታወስ ችሎታን እና ነገሮችን አስቀድሞ የመገመት ችሎታን ያሻሽላል። አንዳንድ ጊዜ ህጻኑ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ፎቶ አንስታችሁ ደብተሩ ውስጥ ልታስቀምጧቸው ትችላላችሁ። በተጨማሪም የህጻኑን ዘመዶች የሚመለከቱ ማናቸውም መረጃዎች ከህጻኑ ጋር ውይይት ተደርጎባቸው ሊመዘገቡ ይገባል።
ይህ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ህጻኑ ስለ እራሱ ያለውን ግንዛቤ ያጠናክራል (“ይገርማል! በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ሩብ ኢንች አድገሀል! እንደዚህ በጣም ትልቅ በመሆንህ ምን ይሰማሀል?”)።
ህጻኑ ከሚያደርጋቸው ነገሮች ውስጥ የትኞቹ የተለመዱ እንደሆኑ እና የትኞቹ ደግሞ ልዩ እና ከሌሎች ህጻናት የተለየ እንደሚያደርጉት መወያየት ጠቃሚ ነው። እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር መስተጋብር ከሚያደርግበት መንገድ ውስጥ ምን የተለመደ ባህሪው እንደሆነ (“እኔን ስታናግረኝ ሁል ጊዜም ትኩረት ትሰጠኛለህ እንዲሁም አይን አይኔን ታየኛለህ፤ ይህ ደግሞ በጣም ያስደስተኛል!”)
የህጻንን እንቅስቃሴ በመቅረጽ ላይ ያለች እንክብካቤ ሰጪ
10 ደቂቃ
- እነዚህ ምክሮች ምን እንድታደርጉ አነሳሷችሁ? በቤት ውስጥ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
- ህጻኑ በጥሩ መልኩ የግል ጊዜ እና ቦታ እንዳለው እና ቤቱ እንደሆነ ይበልጥ እንዲሰማው ለማድረግ የሚረዱ መልካም ተሞክሮዎች፣ ልማዶች ወይም ሀሳቦች አሏችሁ?
- ህጻኑ ይበልጥ ስለእራሱ ግንዛቤ እንዲኖረው እና በቤተሰቡ ውስጥ ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር በምን መልኩ መስተጋብር እንደሚያደርግ እንዲገነዘብ ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው?
- ልጁ ራሱ ስለሚያሳየው ባህሪ እና ይህ ባህሪ በሌሎች ሰዎች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ይበልጥ ግንዛቤ እንዲኖረው ልጃችሁን የሚረዱት የትኞቹ እንቅስቃሴዎች ናቸው ብላችሁ ታስባላችሁ? ለምሳሌ፡- በየቀኑ ዳያሪ መጻፍ፣ ሞባይል ስልካችሁ ላይ ቪዲዮ መቅረጽ፣ በመስታወት መጫወት፣ ወዘተ።