ክፍለ ጊዜ 10/21
ገጽ 6/7 ርዕስ መ፡- በአደራ ቤተሰቡ የግንኙነት መረብ ውስጥ ያሉ ግንኙነቶችን ማጠናከርርዕስ መ፡- በአደራ ቤተሰቡ የግንኙነት መረብ ውስጥ ያሉ ግንኙነቶችን ማጠናከር
ምን አልባት ህጻኑ የቅርብ ግንኙነት ውስጥ ከመሆን ጋር በተያያዘ ችግር ስላለበት አብዛኛውን ጊዜ የአደራ ቤተሰብ ወላጆቹ ላይ ብስጩ ቢሆንም ለምሳሌ በት/ቤቱ ይበልጥ ግልጽ የሆነ መዋቅር በመኖሩ እና ከስሜት አንጻር ብዙ የሚጠበቅበት ነገር ስለሌለ በዚያ ተመሳሳይ ችግር ላይኖርበት ይችላል። ወይም ደግሞ በአደራ ቤተሰቡ ውስጥ ባለው አነስተኛ አካባቢ ውስጥ እና የዕለት ተግባራት ላይ ጥሩ ቢሆንም በት/ቤቱ ውስጥ ብዙ ሰዎች ካሉ፣ ብዙ ጫጫታ ካለ እና ብዙ የተለያዩ መምህራን ካሉ ግራ ሊጋባ እና የተዘበራረቀ ነገር ሊታይበት ይችላል።
በዚህም የተነሳ ለምሳሌ የአደራ ቤተሰብ ወላጆች እና የት/ቤት መምህራን በጣም የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሯቸው እና ምን አልባትም ህጻኑ የሚያስፈልገው ምንድን ነው የሚለው ላይ ባይስማሙ በጣም የሚጠበቅ ነው። በተጨማሪም የአደራ ቤተሰብ ወላጆቹ ዘመዶች ህጻኑን በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች ሊኖሯቸው ይችላል፡-“ልጁ ላይ በጣም ጥብቅ ናችሁ” ወይም “ከራሳችሁ ልጆች በላይ በጣም ለእሱ ታስባላችሁ” ወይም “እኔ ልጁ ላይ ምንም ችግር አላየሁበትም፤ እናንተ ለምንድን ነው ችግር ያያችሁበት?” ሊሉ ይችላሉ።
የመጀመሪያው ምሳሌ ላይ የቀረበው የአደራ ቤተሰብ የአደራ ቤተሰቡ የግንኙነት መረብ ውስጥ ያሉ አባላት የአደራ ቤተሰብ ልጃቸውን እንዲገነዘቡ እና አብረው እንዲሰሩ ምን እንዳደረጉ እንደሚከተለው ያስረዱናል፡-
“ከአዲስ ሰዎች ጋር ሲሆን ሁል ጊዜም በጣም ተግባቢ ነበር እንዲሁም ካገኘው ሰው ሁሉ ጋር (መንገድ ላይ ከሚያያቸው ፈጽሞ የማያውቃቸው ሰዎች ጋርም ሳይቀር) መስተጋብር ያደርግ ነበር። ሰዎች ሁል ጊዜም እንደሱ ያለ ደስ የሚል ልጅ አይተው እንደማያውቁ ይነግሩን እና በጣም ጥብቅ ሆናችሁበታል ብለው ይወቅሱን ነበር። ነገር ግን ልክ ትምህርት ሲጀምር እንዳደረገው ረዘም ላለ ጊዜ ከተመሳሳይ ሰዎች ጋር ከቆየ ያለበት ችግር ግልጽ እየሆነ ይመጣል። የፈለግኩት ካልሆነ ብሎ ይበሰጫጭ ነበር፣ ሌሎች ህጻናት ላይ ጉልቤ ይሆን ነበር፣ ተረጋግቶ መቀመጥ አይችልም ነበር እና በጣም ቀላል ስለሆኑ ውሳኔዎች ሳይቀር ከመምህሩ ጋር ይጨቃጨቅ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መምህሩ እኛ እንዴት እንደምናሳድገው እንዳላወቅንበት መናገር ጀምራ ነበር። ሁል ጊዜም ሁሉም ሰው ላይ የሚከሰተው ይህ ነበር፡- መጀመሪያ ይወዱት እና ከዚያ የሚቀራቡበት ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ በባህሪው ይደናገጣሉ። ከእኛ ጋር ብዙ ውይይት ካደረገች በኋላ ግን ችላ የተባሉ ህጻናት ያሉባቸውን ችግሮች መገንዘብ የጀመረች ሲሆን በመጨረሻም ተጋግዘን መሥራት ጀምረናል። ጠዋት ላይ እንዴት እንደምናስረክባት እና ችግሮች ካሉ እንዴት ወዲያውኑ እንደምንደዋወል ዕቅድ አወጣን። አሁን በጣም በጥሩ ሁኔታ ተጋግዘን በመሥራት ላይ ነን። እሱም ተጋግዘን እንደምንሰራ እና ሁል ጊዜም ጥበቃ እና እገዛ እንደሚደረግለት ያውቃል።”
አስተያየት የሚሰጥባቸው እና ውይይት የሚደረግባቸው ጥያቄዎች
10 ደቂቃ
- ከእናንተ የአደራ ቤተሰብ ልጅ ጋር በተያያዘ በእንክብካቤ ሰጪዎች መካከል እነዚህን ችግሮች አስተውላችኋል?
- ህጻኑ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚያሳያቸውን ባህሪዎች በግንኙነት መረቡ ውስጥ ያሉት ሰዎች በሙሉ እንዲገነዘቧቸው ከማድረግ ጋር በተያያዘ ምን ችግሮች ገጥመዋችኋል?
በግንኙነት መረቡ ውስጥ ያሉት ሰዎች ተጋግዘው እንዲሰሩ ለማድረግ የሚረዱ ተሞክሮዎች፣ ሀሳቦች ወይም ምክሮች አሏችሁ?
ግንዛቤ የመገምገሚያ ነጥቦች
- ከቤተሰብ መሰል እንክብካቤ ውጭ የተመደቡ ህጻናት እና ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ለራሳቸው ዝቅተኛ ግምት የሚኖራቸው እና የጎዳና ተዳዳሪ እንደሆኑ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?
- ህጻኑ የአደራ ቤተሰቡ የራሱ ቤተሰብ እንደሆነ እና የራሱ የሆነ ጊዜ እና ቦታ እንዳለው እንዲሰማው ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
- ህጻኑ ስለ የዕለት ተዕለት መስተጋብሮች እና በዕለት ተዕለት ሁኔታዎች ውስጥ ምን ዓይነት ባህሪ ማሳየት እንዳለበት እንዲማር በምን መልኩ መሥራት ትችላላችሁ?
- በግንኙነት መረቡ ውስጥ ያሉት ሰዎች በሙሉ ህጻኑን ተመሳሳይ በሆነ መልኩ እንዲገነዘቡት ከማድረግ ጋር በተያያዘ ያሏችሁ ተሞክሮዎች ምን ይመስላሉ? ይህን ለማጠናከር እንዴት መስራት ትችላላችሁ?