ክፍለ ጊዜ 14/21

ገጽ 3/7 ከልጅነት ወደ አዋቂነት መሸጋገር

ከልጅነት ወደ አዋቂነት መሸጋገር

አንድ ህጻን ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ሲገባ

ከልጅነት ወደ አዋቂነት ሽግግር የሚደረግበት ወቅት ከፍተኛ አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና የስሜት ለውጦች የሚከሰቱበት ወቅት ነው። ሰውነት በፍጥነት ሆርሞን በማምረቱ የተነሳ አንጎል እና ሰውነት በጥቂት አመታት ውስጥ የሚያድጉ በመሆኑ ህጻኑ የሚቀጥለውን ትውልድ መፍጠር ወደሚችል ጎልማሳ ሰው ይቀየራል። ይህ ከልጅነት ወደ አዋቂነት የሚደረግ ሽግግር ጉርምስና ተብሎ ይጠራል። ከስነ-ልቦና እና ከማህበራዊ አንጻር በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች የግድ በሂደት ከእንክብካቤ ሰጪዎቻቸው ጋር መራራቅ እና መለያየት፣ ራሳቸውን ችለው የራሳቸውን ማንነት መገንባትን መልመድ እና አዲስ ማህበራዊ ትስስር መፍጠር ይኖርባቸዋል። እንክብካቤ ሰጪዎችም እንክብካቤ እና ጥበቃን ከአክብሮት ጋር አመጣጥነው ማስኬድ የሚችሉባቸውን መንገዶች ማግኘት እና የራሳቸውን ህይወት እንዲመሩ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆችን ማገዝ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ለሁለቱም ወገኖች ከባድ ጊዜ ነው።

በጉርምስና ወቅት ሌሎች በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች ግሩፕ አባል መሆን ከቤተሰብ ጋር ካለው ግንኙነት በላይ ድንገት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይሆናል እንዲሁም በት/ቤት የሚያስፈልጉት ነገሮች ይቀየራሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች ከጉርምስና ጋር ተያይዞ የሚመጣ ራስን የመቻል ተፈጥሮአዊ ፍላጎት ሊሰማቸው ይችላል። እንደዚያም ሆኖ ግን ከዚህ ጎን ለጎን የወላጅ እንክብካቤ እና አመራር ያስፈልጋቸዋል። በሰውነታቸው ላይ የሚከሰቱ አካላዊ ለውጦችን እና አዳዲስ ስሜቶችን መልመድ ስለሚኖርባቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ላሉ ልጆች ከባድ ጊዜ ነው። እንክብካቤ ሰጪዎቻቸውም እንክብካቤ የሚሰጡባቸው አዳዲስ መንገዶችን ማግኘት እና ልጆቻቸው ሲለወጡ እና አዋቂዎች ሲሆኑ ማገዝ ይኖርባቸዋል። ለብዙ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች ጉርምስና የማይገፋ ተራራ ሊሆንባቸው ይችላል።

የአደራ ቤተሰብ እናት እንደመሆኔ መጠን የአደራ ቤተሰብ ልጄ ከሆነችው ከክሪስቲና አገኝ የነበረውን መደበኛ ታዛዥነት እና እምነት ትቼ መቀጠል ከባድ አጣብቂኝ ነው። አሁን እኔን ማዳመጥ አቁማለች፣ ትተቸኛለች እንዲሁም መቼ ተመልሳ እንደምትመጣ ሳትናገር ትወጣለች። የራሷን ህይወት እንድትኖር ለማገዝ ስል የተወሰነ ነጻነት ልሰጣት እፈልጋለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ በዙሪያዋ ስላሉት አደጋዎች ግንዛቤ እንደሌላት እና እነዚህ አደጋዎች መኖራቸውን አውቃ ራሷን ለመጠበቅ የሚያስችል ብስለት እንደሌላት ይታየኛል።

ጉርምስና እና በእንክብቤ ላይ ያሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች

በእንክብካቤ ላይ ያሉ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ ትንሽ እያሉ የመለያየት ሰቆቃ፣ ወላጆቻቸውን ማጣት ወይም አካላዊ ችላ መባል የደረሰባቸው ናቸው። እነዚህ ተሞክሮዎች ከልጅነት ወደ አዋቂነት የሚደረገውን ሽግግር የባሰ ፈታኝ ሊያደርጉት ይችላሉ። ራስን የመቻል ፍርሀት ወይም በህይወት ውስጥ በትንሽ ዕድሜ ላይ እያሉ እንደ አዋቂ መሆን የተለመዱ ችግሮች ናቸው። ድንገት የሚከሰቱ የስሜት ለውጦች ከወትሮው በላይ በጣም ሊጠነክሩ ይችላሉ። በዚህ ወቅት መቀራረብ የሚለው ይቀየር እና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው ልጅ እንዲማር እና ራሱን ችሎ የአዋቂ ህይወት እንዲመራ ሲባል በቤት ውስጥ ካለው አስተማማኝ መሰረት ጋር አዎንታዊ በሆነ መልኩ መራራቅ እና መለያየት የሚችለው እንዴት ነው በሚለው ጥያቄ ይተካል። ጨቅላ ህጻናት እያሉ የከፋ ጥቃት፣ መጥፎ አያያዝ ወይም ንፍገት የደረሰባቸው ልጆች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጉርምስና የሚገቡት ከዕድሜአቸው ቀድመው ነው እንዲሁም አንዳንዶቹ ላይ 8-10 ዓመታቸው እያለ ጭምር ፈጥኖ ይከሰታል። ይህም ያለዕድሜ ወሲብ የመጀመር እና የማርገዝ አደጋ እንዲጨምር ያደርጋል።

እንክብካቤ ሰጪዎች የእንክብካቤ አሰጣጥ ዘይቤአቸውን ማስተካከል የሚችሉት እንዴት ነው?

ጉርምስና መጣ ማለት የእንክብካቤ ሰጪው ዘይቤ ከትዕዛዝ በሕጎች እና በነጻነት ዙሪያ ውይይት፣ ድርድሮችን እና ስምምነት ወደማድረግ መቀየር አለበት ማለት ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ላሉ ልጆች ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ከማሳለፍ በላይ ከጓደኞቻቸው እና ከክፍላቸው ልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይበልጥ ቦታ አለው። ይህን መገንዘብ እና መቀበል አስፈላጊ ነው። ይህ እራስን ወደመቻል የሚደረግ ተፈጥሮአዊ እርምጃ በመሆኑ መቆጣት፣ መስበክ እና መቆጣጠር መስራት ያቆማል። ስለዚህ አንድ እንክብካቤ ሰጪ ከዚያ በተጨማሪ አለማማጅ እና አጋር መሆን አለበት፡- በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው ልጅ ከጓደኞቹ ጋር ባለው ግንኙነት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች የሚያዳምጥ እና ስለዚያ የሚያወራ ሰው መሆን ማለት ነው። ውይይቶቹ በራሳቸው እንዲሁም ነገሮችን የመቀበል ባህሪ ማሳየት በጣም የሚረዳ በመሆኑ (እና አንዳንድ ጊዜም የሚያስፈልገው ብቸኛ እርዳታም ሊሆን ስለሚችል) ሁል ጊዜም መፍትሄዎችን ማምጣት አይኖርባችሁም። ለምሳሌ አንድ ወጣት ስለ የአደራ ቤተሰብ ወላጆቹ ያለውን ትውስታ እንደሚከተለው ገልጾታል፡- ምንም ያህል ግራ ብጋባ ወይም ምንም ያህል ብቃወማቸውም ሁል ጊዜም ስለ ማንኛውም ነገር ላናግራቸው እችል ነበር። ዝም ብለው ያዳምጡኝ ነበር እንዲሁም ፈጽሞ አይወቅሱኝም ነበር። ዋናው ነገር እንክብካቤ ሰጪው ርህራሄ በተሞላበት፣ በተረጋጋ እና ቁርጠኛ በሆነ መልኩ ነገሮችን የሚረዳ መሆኑን ማሳየቱ እና እንክብካቤ ሰጪዎች እና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች ውሳኔዎችን እና የቤቱን ሕጎች በተመለከተ መስማማታቸው ነው።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ካለ ልጃችሁ ጋር ጥሩ ግንኙነት መመስረት የምትችሉበት መንገድ

በጉርምስና ወቅት በልጅ እና በእንክብካቤ ሰጪ መካከል ያለው ግንኙነት ይቀየራል። ጭቅጭቆች እና ግጭቶች መከሰታቸው አይቀርም፤ ይህም ራስን ወደመቻል የማደግ አንድ አካል ነው። መቀራረብ ቁጣን የሚቀሰቅስበት ዕድሜ ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው ልጅ ከሌሎች ወጣቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ሊጀምር እና ለዚህ ግሩፕም ይበልጥ ታማኝ ሊሆን ይችላል። ይህም ወደ ሀፍረት እና ከእንክብካቤ ሰጪዎች ወደመነጠል፣ አላዳምጥም ወደማለት ወይም ከአንክብካቤ ሰጪው ጋር ካለማቋረጥ ወደመጨቃጨቅ ሊያመራ ይችላል። በዚህ ረገድ አብዛኛው ነገር የሚወሰነው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው ልጅ መስመሮችን ማለፍ ሲጀምር እንክብካቤ ሰጪው ምላሽ በሚሰጥበት መንገድ ይሆናል።

በጉርምስና ወቅት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው ልጅ ስለራሱ አዲስ እና ራሱን የቻለ ግንዛቤ መፍጠር ይኖርበታል እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ እንደ ህጻን ጥገኛ በመሆን እና ከእንክብካቤ ሰጪው ጋር ርቀት በመፍጠር ራሱን የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር በመሞከር መካከል ይመላለሳል። ይህ ጤናማ ቢሆንም እንክብካቤ ሰጪዎች ላይ ብዙ ጥርጣሬ ይፈጥራል፡- እንክብካቤ ሰጪው ገደቦችን እና ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ ያለበት መቼ ነው፤ አንድ ሰው እምነት ማሳየት እና ይበልጥ ኃላፊነት መስጠት ያለበትስ መቼ ነው?

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው ልጅ ችላ በመባሉ፣ አሰቃቂ ሁኔታዎች ውስጥ በማለፉ ወይም ሰውን በማጣቱ የተነሳ የህይወቱ መጀመሪያ ላይ ከባድ ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ከሆነ ጉርምስናው ለእንክብካቤ ሰጪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። እንክብካቤ እና አመራር ከመስጠት ጎን ለጎን በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው ልጅ የራሱን ውሳኔ እንዲወስን እና ራሱን እንዲያስተዳድር መደገፍ የምትችሉት እንዴት ነው?

ቁጥጥርን በአስተማማኝ እና ግልጽነት ባለበት ግንኙነት መተካት

አንድን ህጻን ወደ አዋቂነት በሚያደርገው ሽግግር መደገፍ የሚቻልበት ዋነኛው መንገድ ጠንካራ እና አዎንታዊ ግንኙነትን በመገንባት ነው። ከእንክብካቤ ሰጪአቸው ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍ ሁኔታቸው እንደሚቀንስ፣ ዝቅተኛ የአእምሮ ጤና ችግሮች እንዳሉባቸው እንዲሁም የተሻሉ ማህበራዊ ክህሎቶች እና ጭንቀትን የመቋቋሚያ ዘዴዎች እንዳሏቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ። በተጨማሪም ከእንክብካቤ ሰጪዎቻቸው ጋር ጠንካራ እና ግልጽ ውይይቶችን የሚያደርጉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች መጠጥ የመጠጣት፣ እጾችን ያለአግባብ የመጠቀም እና አስተማማኝ ያልሆኑ ወሲባዊ ድርጊቶች ውስጥ የመሳተፍ ሁኔታቸው ዝቅተኛ ነው።

በእንክብካቤ ሰጪው እና በልጁ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ልጁ ችግር ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ እንክብካቤ ሰጪው ከጎኑ መሆን እና ስሜቱን መገንዘብ አለበት። አንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለ ልጅ አስተማማኝ ቅርርብ እንዳለው እንዲሰማው ድክ ድክ ከሚል ህጻን እኩል አካላዊ ቅርርብ አያስፈልገውም። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ላሉ ልጆች አስፈላጊ የሆነው ነገር እንክብካቤ ሰጪዎቻቸው ድጋፍ ማድረጋቸው እና ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው ነው። አትራቁ ነገር ግን ክፍተት ስጧቸው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለ ልጃችሁ ሲፈልጋችሁ በማንኛውም ጊዜ መገኘትን እና አነስ ያሉ እና ማስተናገድ የሚችላቸውን ስጋቶች እንዲጋፈጥ ማበረታታትን አትርሱ። ይህም በኋላ ላይ በህይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመቋቋም ይረዳዋል።

ኬንያ ውስጥ በኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ውስጥ ካደጉትን እና ከልጅነት ወደ ዕውቀት ከመሸጋገር ጋር በተያያዘ ያላቸውን ተሞክሮ ከሚያጋሩት ከፖል እና ከዊልኪስታ ጋር የተደረገውን ይህን አጭር ቃለ መጠይቅ ተመልከቱ። ትልቅ ህልም ስለማለም ያወራሉ እንዲሁም ልባችንን መከተል እና ህልማችንን ለማሳካት መሞከር አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ። በተጨማሪም ጉርምስና ላይ ላሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች ምክራቸውን ይለግሳሉ እንዲሁም እንክብካቤ ሰጪዎች በጣም ሁነኛ በሆነ መልኩ ሊደግፏቸው ስለሚችሉበት መንገድ ሀሳባቸውን ያካፍላሉ።