ክፍለ ጊዜ 14/21

ገጽ 6/7 ከቁጥጥር ወደ መስማማት

ከቁጥጥር ወደ መስማማት

እንብካቤ ሰጪዎቻቸው በባህሪያቸው ያለመቆጣትን እና ገደቦችን እና መታለፍ የሌለባቸው መስመሮችን ጥብቅ በሆነ መልኩ ማስከበር መቀጠልን በአግባቡ አጣጥመው ማስኬዳቸው ጉርምስና ላይ ላሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች አስፈላጊ ነው። የትኞቹ ሕጎች ድርድር የሚደረግባቸው ናቸው እና የትኞቹ የቤቱ ሕጎች ደግሞ ለድርድር የማይቀርቡ ናቸው የሚለው ላይ በጣም ግልጽ መሆን አስፈላጊ ነው። ልጆች ያስቀማጣችሁትን መስመር ለማለፍ በሚሞክሩበት ወቅት ይህን ማወቅ አስፈላጊ ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች ያስቀመጣችሁትን የማይታለፍ መስመር ለማለፍ መሞከራቸው አይቀርም። ስለዚህ ድርድር ሊደረግባቸው የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው እንዲሁም ለድርድር የማይቀርቡ ነገሮች ምንድን ናቸው የሚለውን ልትገነዘቡ ይገባል።

ማስታወስ ያለብን ጠቃሚ መመሪያ የሚከተለው ነው፡- ምንም ያህል የህጻን ባህሪ እያሳየ ነው ብላችሁ ብታስቡ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለ ልጅን ስታናግሩ ሁል ጊዜም አዋቂ ጎኑን አናግሩ። ሌላኛው ማስታወስ ያለባችሁ ጠቃሚ መመሪያ የሚከተለው ነው፡- የግድ አንዲህ መሆን አለበት አትበሉ፣ እንዲህ ብታደርግስ ብላችሁ አስተያየት አትስጡ ወይም አትጠይቁ! ከዚያ ይልቅ ምክንያቶቻችሁን አስረዱ። ግንኙነታችሁ ስልጣን እና ጥገኝነትን ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ መከባበርንም መሰረት ያደረገ እንዲሆን ያስፈልጋል።

“እኛ እንክብካቤ ሰጪዎችህ ነን፤ አንተ ደግሞ ልጅ ነህ” የሚለው የኃላፊነት ክፍፍል በተፈጥሮ ጉርምስና ላይ ይጠፋል፤ ስለዚህ ተቀናጅተን መሥራት የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶችን ማግኘት አስፈላጊ ነው። ከቁጥጥር ይልቅ ስምምነት ማድረግን መጠቀም ጥሩ ሊሆን ይችላል።

የመልመጃ ሀሳብ፡- የውል ስምምነት ማድረግ
በመጀመሪያ እሱ ሀሳቦቹን እንዲያቀርብ በማድረግ እና የጋራ ውል ላይ በመወያየት እና በመስማማት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ያለው ልጅ በውሳኔ ወስጥ እንዲሳተፍ ዕድል ለመስጠት መዘጋጀት ትችላላችሁ። ለምሳሌ ውጭ ማምሸት የሚፈቀድለት እስከ ስንት ሠዓት እንደሆነ፣ አስቸጋሪ ነገር ከተከሰተ እንክብካቤ ሰጪውን ማናገር እንዳለበት እና ብቻውን የመሆን መብት እንዳለው፣ ወዘተ። ውሉን እንደሚከተለው ልታቀርቡት ትችላላችሁ፡-

 “እያደግክ በመሆኑ በራስህ ብዙ ነገሮችን ማድረግ ትችላለህ። ይህም ማለት በቤት ውስጥ የተወሰኑ ግዴታዎች የሚኖሩብህ ቢሆንም ከዚያ በተጨማሪ አንዳንድ መብቶች ይኖሩሀል ማለት ነው። በየቀኑ ማድረግ ያሉብህን ነገሮች፣ ከጓደኞችህ ጋር ምን ያህል ማምሸት እንደምትችል እና ለምን እንደዚያ ወሰንክ ብለን ሳንከራከር በራስህ እንድትወስን እንደምንፈቅድልህ ጉዳዮች ያሉ ከእኛ የምታገኛቸው ነጻነቶች ምን እንደደሆኑ የሚገልጽ ውል ከአንተ ጋር ማዘጋጀት እንፈልጋለን። በተጨማሪም አንተ ወይም እኛ በዚህ ውል ውስጥ የተስማማንበትን ነገር ሳንፈጽም ብንቀር እንክብካቤ ሰጪዎችህ እንደመሆናችን መጠን ምን ማድረግ እንዳለብን መነጋገር ይኖርብናል። ስለዚህ ውሉን አብረን መጻፍ እንጀምር። ምን ጉዳዮች ላይ መስማማት አለብን የሚለውን በተመለከተ ማቅረብ የምትፈልጋቸው ሀሳቦች አሉ (ለአንተ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው)?”

  • ስምምነት የሚያስፈልግባቸው ሁለት የዕለት ተዕለት ሁኔታዎችን ለማግኘት ሞክሩ።
  • ውሉ ምን ምን ያካተተ እንዲሆን እንደምትፈልጉ ለመጻፍ ወይም ለማሰብ ሞክሩ፤ ነገር ግን ሁል ጊዜም መጀመሪያ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው ልጅ የሚያቀርባቸውን ሀሳቦች ለማዳመጥ ሞክሩ።
  • ስምምነት ከተደረገበት በኋላ ውሉን ቤት ውስጥ የሆነ ቦታ ላይ ግድግዳ ላይ ልትሰቅሉት ትችላላችሁ?

የቡድን ውይይት
15 ደቂቃ

  • በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ካሉ ልጆች ጋር የተያያዘ ሥራ በምትሰሩበት ወቅት በጣም ፈታኝ የሚሆንባችሁ ነገር ምንድን ነው?
  • ስልጣንን እና ሕጎችን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ላለው ልጅ የተወሰነ ነጻነት መስጠትን አመጣጥናችሁ የምታስኬዱት እንዴት ነው?
  • በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለ ልጃችሁ በሚነጫነጭበት ወይም በሚቃወምበት ወቅት እንድትረጋጉ፣ ሩህሩህ እና ምክንያታዊ እንድትሆኑ የሚረዳችሁ ምንድን ነው?