ክፍለ ጊዜ 14/21

ገጽ 4/7 ስለ ጉርምስና በህጻንነት ውይይቶችን ማድረግ መጀመር

ስለ ጉርምስና በህጻንነት ውይይቶችን ማድረግ መጀመር

በጉርምስና ወቅት ለሚከሰቱ ነገሮች ህጻናትን ማዘጋጀት

ጨቅላ ህጻን ወይም ህጻን እያሉ በሚያልፉበት አሰቃቂ ሁኔታ፣ ችላ መባል እና የምግብ እጥረት የተነሳ በአማራጭ የሕጻናት እንክብካቤ ላይ ያሉ ህጻናት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጉርምስና የሚገቡት ከእኩዮቻቸውቀድመው ነው። ወደ ጉርምስና በሚገቡበት ወቅት የእንክብካቤ ሰጪዎቻቸው እገዛ እና አመራር በከፍተኛ ሁኔታ ያስፈልጋቸዋል።

አንድን ህጻን ለጉርምስና ለማዘጋጀት በጣም ጠቃሚ ከሆኑት ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ጉርምስና ከመጀመሩ የተወሰኑ ዓመታት አስቀድሞ ግልጽ ውይይቶችን ማድረግን መለማመድ እና ስለ ጉርምስና ማውራት ነው። ግልጽ ውይይቶችን ለማድረግ መሰረቱ በልጅነት ወቅት መተማመንን እና ግልጽ ውይይቶችን መልመድ ነው። ህጻናት የዕለት ተዕለት ህይወትን በተመለከተ ስለሚያስቧቸው ነገሮች እና ስለሚሰሟቸው ስሜቶች በየቀኑ ውይይቶችን ማድረግን መልመድ አለባቸው፡- ትምህርት ቤት ውስጥ ስለተፈጠሩ ነገሮች፣ ስለጓደኝነቶቻቸው፣ ስለግል ንጽህና፣ ወዘተ ማለት ነው። ይህም በማንኛውም ጊዜ ሊደረግ ይችላል፡- ለምሳሌ ከሠዓት በኋላ እረፍት ላይ ወይም ማታ ላይ ምግብ እየተመገቡ። በዚህ መልኩ ህጻናት ሀሳባቸውን ለእናንተ ማካፈልን ይለምዳሉ፤ ይህም እንደ ጉርምስና ስላሉ የግል ጉዳዮች ለመወያየት እንደ መሰረት ያገለግላል።

ህጻኑን ከትንሽ ዕድሜ (8-10 ዓመት) ጀምሮ ሰውነቱ እና አእምሮው መቀየር ሲጀምር መጠበቅ ስላሉበት ነገሮች ብታዘጋጁት አሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሲገባ የሚኖረውን ህይወት በጣም ልታቀሉለት ትችላላችሁ። አሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ መግባት ለልጆች አስፈሪ እንዲሁም አጓጊ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ሰውነታቸው፣ ስሜቶቻቸው እና እሴቶቻቸው በምን መልኩ እንደሚቀየሩ እንዲገነዘቡ ማገዝ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ የሆነ ቀን ጉርምስና ሲከሰት የበለጠ በጣም እንዲረጋጉ ይረዳቸዋል።

ሰውነት ላይ ምን ዓይነት ለውጦች እንደሚከሰቱ፣ የተቃራኒ ጾታ አመለካከቶች እንዴት ሊቀየሩ እንደሚችሉ እና ግንኙነታችሁ እንዴት ሊቀየር እንደሚችል በዕለት ተዕለት ውይይቶች ውስጥ ማስረዳት ትችላላችሁ። ይህም አብራችሁ እየሰራችሁ እያላችሁ፣ እረፍት ላይ እያላችሁ ወይም ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ እያላችሁ ሊደረግ ይችላል።

በተጨማሪም እነዚህን ውይይቶች እንደ የቤተሰብ ጨዋታ ሁሉም ዕድሜ ላይ ካሉ ልጆች ጋር ማድረግ የሚለውን ልታስቡበት ትችላላችሁ። ይህን ማድረግ በዕድሜ አነስ ያሉ ልጆች ጉርምስና ማለት ምን እንደሆነ ለመገንዘብ እንዲቀላቸው ያደርጋል እንዲሁም በቤተሰቡ ውስጥ አሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ካሉ ልጆች ሊማሩ ይችላሉ። በዕድሜ አነስ ያሉ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በቤተሰቡ ውስጥ ያሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች ከእነሱ ጋር የመጫወት ፍላጎታቸው እንደጠፋ ይሰማቸዋል እንዲሁም የነበራቸው ጓደኝነት ይናፍቃቸዋል። ስለዚህ በቤተሰቡ ውስጥ ያለ አንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለ ልጅ ለምን ነጭናጫ እንደሆነ ልታስረዷቸው ትችላላችሁ። በእነዚህ ግልጽ ውይይቶች ላይ ህጻኑ እንደምትገነዘቡት እና እንደማትፈርዱበት እንዲሰማው የሚያደርግ አስተማማኝ እና ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ትችላላችሁ።

በተጨማሪም ህጻኑን በአንዳንድ ሥራዎቻችሁ ውስጥ በማሳተፍ ለጉርምስና እና ለአዋቂነት ልታዘጋጁት ትችላላችሁ። ይህን ማድረግ የሚቻልባቸው ሁለት መንገዶች አሉ። አንደኛው መንገድ ህጻኑ እያደገ ሲመጣ የዕለት ተዕለት ሥራዎችን የማከናወን ኃላፊነት ይበልጥ እየወሰደ እንዲመጣ በማድረግ እና በዕለት ተዕለት ተግባራት ዙሪያ በማሰልጠን ነው። ይህም ማለት የአገልግሎት ክፍያዎችን መክፈል፣ የቤቱን በጀት ማዘጋጀት እና ግዢ መፈጸም፣ ብስክሌት ወይም መኪና መጠገን፣ ወዘተ ማለት ነው። ሌላኛው መንገድ ደግሞ እንደ ወላጅ መሆንን መቀነስ እና ከዚያ ይበልጥ ሰውነት ላይ ምን ዓይነት ለውጦች እንደሚከሰቱ የሚያውቅ፣ እንዴት አይን አፋርነትን ማስወገድ እና የሚወዱትን/የሚወዷትን ልጅ ማነጋገር እንደሚቻል የሚያውቅ፣ ራሱ የጉርምስና ዕድሜ ላይ እያለ የሰራቸውን ስህተቶች እንደ እንክብካቤ ሰጪ የሚያስረዳ፣ ራስን ከመጥፎ ጓደኛ እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል የሚያውቅ፣ ወዘተ ልምድ ያለው የውይይት አጋር መሆን ነው።

ህጻናትን ስለ ጉርምስና በምናነጋግርበት ወቅት አስፈላጊው ነገር ምንድን ነው?  

እነዚህ ውይይቶች ላይ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበራችሁበት ወቅት ራሳችሁ ስለነበሯችሁ ተሞክሮዎች ሁለት ሁለት በመሆን ያደረጋችሁት ውይይት ላይ ያነሳችኋቸውን ሀሳቦች መጠቀም ትችላላችሁ። ህጻናት እነዚህን ታሪኮች መስማት ይወዳሉ። ምን ከብዷችሁ እንደነበር እና ምንም እንኳን ብዙ መሰናክሎች ቢያጋጥሟችሁም አንዴት ያንን ተቋቁማችሁ አዋቂ እና የበሰለ ሰው መሆን እንደቻላችሁ ማለት ነው። እባካችሁ የአሥራዎቹ ዕድሜያችሁ ከባድ እና ግራ የሚያጋባ የነበረ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ችግሮች እና ጭንቀቶች የአዋቂነት ዕድሜ ላይ ስትደርሱ እንደጠፉ አጽንዖት ሰጥታችሁ ግለጹ። ይህ ያጽናናቸዋል።

ጉርምስና ውስጥ ያሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች እንክብካቤ ሰጪዎቻቸው ላይ ሊናደዱ እና ሊያዝኑ እንደሚችሉ ለህጻኑ ንገሩት። ይህም ራስን ለመቻል የመሞከር አንድ ጤናማ አካል መሆኑን እና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለውን ልጅ እንደማትወቅሱት እና እንደማታዝኑበት ለህጻኑ ንገሩት።

ከዚህ በተጨማሪ በቤተሰቡ ውስጥ ምን ዓይነት ባህሪ ማሳየት ያስፈልጋል የሚለውን ስለሚመለከቱ ሕጎች ትወያያላችሁ። ጠንክረው አልኮልን፣ ማጨስን እና መጥፎ ጓደኝነት ውስጥ መግባትን አልፈልግም በማለታቸው ጥሩ ህይወት በመኖር ላይ ስላሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች በማውራት ልጁን አግዙት። በተጨማሪም ዝም ብለው እናንተ ያወጣችኋቸውን ሕጎች ከማክበር ይልቅ በንቃት ተሳትፎ ማድረግን እና መስማማትን እንዲማሩ መስማማት በምትችሉባቸው የቤቱ ሕጎች ዙሪያ ሀሳቦችን እንዲያቀርቡ ጠይቋቸው።

ምን አልባት ህጻናቱ አሁን ስለ ጉርምስና የማውራት ፍላጎት አይኖራቸው ይሆናል። ነገር ግን ያወራችሁትን ነገር ስለሚያስታውሱት የሆነ ቀን አሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሲገቡ በእናንተ ለመተማመን እንዲቀላቸው ያደርግላቸዋል።

የመልመጃ ሀሳብ፡- ጥሩ ውይይት
በቅርቡ የአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገቡ ልጆች አሏችሁ? እባካችሁ ከልጅነት ወደ አዋቂነት ስለሚደረገው ሽግግር እንዴት ልታናግሯቸው እንደምትችሉ አቅዱ። በዚህ ረገድ የተወሰኑ ሀሳቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፤ እባካችሁ የራሳችሁን ሀሳብ ተጠቀሙ እና ጻፏቸው።

ልጆቻችሁን ከትንሽ ዕድሜአቸው ጀምሮ ግልጽ ውይይቶችን እንዲለምዱ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
ካሳለፋችሁት፣ ይሰማችሁ ከነበረው እና ታስቡ ከነበረው ነገር ጋር በተያያዘ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያላችሁ የነበራችሁን ተሞክሮ የሚገልጹ አንድ ወይም ሁለት ታሪኮችን ፈልጋችሁ አግኙ።
ምን አልባት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያላችሁ የተነሳችኋቸው ማሳየት የምትችሏቸው ፎቶዎች አሏችሁ?
በጉርምስና ወቅት ስሜታቸው ምን ያህል ሊቀያየር እንደሚችል እና አንድ ሰው እንዴት አንዳንድ ጊዜ በጣም ብቸኝነት ሊሰማው እና ከደቂቃ በኋላ ደግሞ በጣም ደስታ ሊሰማው እንደሚችል ለህጻናቱ ልትነግሯቸው ትችላላችሁ?
የእኩዮቻቸው ግሩፕ ለእሱ ስለሚኖረው ትልቅ ቦታ እና ከእነሱ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ መፈለጉ የሚገባችሁ ስለመሆኑ ከልጁ ጋር ተወያዩ እንዲሁም አዳምጡት።