ክፍለ ጊዜ 15/21

ገጽ 2/7 በእንክብካቤ ውስጥ ስላለፉ ወጣቶች ጥናቶች ምን ይላሉ

በእንክብካቤ ውስጥ ስላለፉ ወጣቶች ጥናቶች ምን ይላሉ

ከእንክብካቤ ወደ አዋቂነት ህይወት የሚደረገው ሽግግር ረጅም ጊዜ የሚፈጅ የዕድገት ሂደት መሆኑን መረዳት
ከእንክብካቤ የሚወጡ ወጣቶች ከእንክብካቤ ከወጡ በኋላ በሚኖራቸው ስኬታማ የመሆን ወይም ያለመሆን ሁኔታ ላይ በዓለም ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች ይህ ወቅት ለወጣቶች በጣም ወሳኝ የሆነ ጊዜ እንደሆነ ያሳያሉ። ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ውስጥ በፍቅር እና በእንክብካቤ ላላደጉ በርካታ ወጣቶች ወደ ማህበረሰቡ እና ወደመጡበት ባህል መመለስ ወይም ሽግግር ማድረግ በጣም ፈታኝ ተሞክሮ ነው። ምንም እንኳን የሚሳካላቸው በርካታ ወጣቶች ቢኖሩም መጨረሻ ላይ የጎዳና ተዳዳሪ ወይም ዕድሜ ልካቸውን ሥራ አጥ የሚሆኑ ወይም የወንጀል እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚገቡም በጣም ብዙ ወጣቶች አሉ። በእንክብካቤ ውስጥ ያለፉ ወጣቶችን ተሞክሮ ማዳመጥ አለብን፡- በማህበረሰብ ውስጥ የአዋቂ ኑሮ ወደመኖር የሚደረገው ሽግግር የሚከሰተው በጣም በድንገት ነው ይላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ከእንክብካቤ መውጣትን የምናስበው ከእንክብካቤ እና ጥበቃ ራስን ችሎ ወደመኖር የሚደረግ አንድ ሽግግር አድርገን ነው። አንድ አፍሪካዊ ተመራማሪ እንዳሉት ይህ አስተሳሰብ አይጠቅምም። ምክንያቱም፡- ወጣቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ የሚቻለው እንክብካቤ ከሚጀምሩበት ጊዜ አንስቶ ዝግጅት በማድረግ እና ከእንክብካቤ ከወጡ በኋላ እርስ በርስ መደጋገፍ ያለበት አዲስ ማህበራዊ ትስስርን በመገንባት ብቻ ነው። ከእንክብካቤ መውጣት ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ሂደት ነው፡- ከህጻንነት ጊዜ ጀምሮ ዝግጅት ማድረግን ያካተተ የረጅም ጊዜ ዕቅድ እና ከእንክብካቤ ከወጡም በኋላ የሚሰጥ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲኖር በእንክብካቤ ውስጥ ላለፉ ወጣቶች በተደረጉት ቃለ መጠይቆች ላይ ወጣቶች ይጠይቃሉ። የምትገኙበትን ሁኔታ መሠረት በማድረግ ከልጅነት እስከ እንክብካቤ መውጣት ድረስ ላሉት ሶስት ምዕራፎች የሚረዳ እውቀትና ሀሳብ ይቀርብላችኋል። ለእያንዳንዱ ምዕራፍ አንድ የሥራ ዕቅድ ለማዘጋጀት ወይም አንደኛው ላይ ለማተኮር ልትወስኑ ትችላላችሁ። የምታደርጉትን ዝግጅት እና ድጋፍ እንዴት ማሻሻል እንደምትችሉ ለማቀድ በመጀመሪያ የሚከተለውን እንወቅ፡- በምስራቅ አፍሪካ በእንክብካቤ ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ያሉባቸው ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
በምስራቅ አፍሪካ በእንብካቤ ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ያሉባቸውን አራት ዋና ዋና ተግዳሮቶች መገንዘብ

በእንክብካቤ ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ተቋቁመው ለማለፍ ድጋፍ የሚጠይቁባቸው አራት ዋና ዋና ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው በእንክብካቤ ውስጥ ካለፉ ወጣቶች እና ከአፍሪካ ተመራማሪዎች ጋር ያደረግናቸው ቃለ መጠይቆች ይጠቁማሉ። በተጨባጭ በዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን በህጻንነት መማር ያስፈልጋቸዋል። ከኤስ ኦ ኤስ እናቶች ወይም ከአደራ ወላጆች ጋር ለመለያየት እገዛ ያስፈልጋቸዋል እንዲሁም ከእንክብካቤ ከወጡ በኋላ የሌሎች ሰዎች ድጋፍ እና አመራር ያስፈልጋቸዋል። በማህበራዊ ትስስሮች ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር መገናኘት እንዲችሉ (ማለትም ከትውልድ ቤተሰባቸው፣ ከማህበራዊ ሠራተኞች፣ ከሥራ ቦታዎች እና በእንክብካቤ ውስጥ ካለፉ ሌሎች ወጣቶች ጋር መገናኘት የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ) እገዛ ያስፈልጋቸዋል። 

ጥናቶችን እና ቃለ መጠይቆችን በምናደርግበት ወቅት በእንክብካቤ ውስጥ ያለፉ ወጣቶች የሚጠይቁን ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

“ከምተማመንበት መኖሪያዬ ከወጣሁ በኋላ የሚሰማኝን የመለያየት ስሜት ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?”

  • ወጣቶች ከእንክብካቤ ከወጡ በኋላ በህይወት ውስጥ ስኬታማ መሆን ያለመሆናቸውን የሚወስኑት በጣም ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች፡- ከአደራ እናታቸው ወይም ከአደራ አሳዳጊዎቻቸው ጋር ጥልቅ የስሜት ቅርርብ ኖሯቸው ማደጋቸው እና ከወንድም እና እህቶቻቸው ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸው ነው። ለወጣቶች ይህን ቤተሰባዊ መሰረት መሰናበት ፈታኝ ነው። በጨቅላነት ዕድሜ የነበረ የመለያየት ስቃይ እንደገና ሊቀሰቀስ እና ከፍተኛ መረበሽ እና ጭንቀት ሊፈጥር ይችላል። በእንክብካቤ ውስጥ ያለፈ አንድ አፍሪካዊ ወጣት እንዲህ ሲል ገልጾታል፡- “ሁሉም ነገር ይጨልምብኝ እና ፍርሀት ይሰማኛል። ሀዘን ይወረኛል … ስለ መጪው ጊዜ ሳስብ ሁልጊዜም ስለራሴ መጥፎ ስሜት ይሰማኛል”። ከእንክብካቤ ከወጡ በኃላ ከእንክብካቤ ሰጪዎች እና ከመምህራን ጋር የነበሩ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ወሳኝ ግንኙነቶች እና መቀራረቦች አብዛኛውን ጊዜ ይጠፋሉ። የኤስ ኦ ኤስ እናቶች ጡረታ ሲወጡ ወይም የአደራ ቤተሰቡ አዳዲስ ህጻናትን በመንከባከብ ሲጠመድ በእንክብካቤ ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ሀዘን እና ብቸኝነት እንደሚሰማቸው ይገልጻሉ። ከእንክብካቤ ከወጡ በኋላም እንኳን የሚመራቸው ያስፈልጋቸዋል።

“ከእንክብካቤ ከመውጣቴ በፊት ተጨባጭ የሆኑ በዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ የሚያስፈልጉኝን ክህሎቶች ተምሬአለሁ?”

  • ደህንነቱ በተጠበቀ ከባቢ ሁኔታ ውስጥ ማደግ አስተማማኝ መቀራረቦችን ለመመሥረት፣ ትምህርት ላይ ጎበዝ ለመሆን እና ለማህበራዊ ዕድገት ጥሩ ነው። ሆኖም ግን አብዛኛዎቹ በእንክብካቤ ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ህጻን እያሉ እንክብካቤ የተደረገላቸው እና አገልግሎቶች የተሰጧቸው ቢሆኑም በዕለት ተዕለት ተግባራት ውስጥ በንቃት በመሳተፍ መሠረታዊ የህይወት ክህሎቶችን የተማሩ አይደሉም። በመሆኑም ወደ ማህበረሰቡ በሚመለሱበት ወቅት አብዛኞቻቸው ቀጠሮ ለማክበር፣ የባንክ ሂሳባቸውን ለማስተዳደር ወይም በጀት ለማቀድ፣ የሥራ ማመልከቻ ለመጻፍ፣ ወይም ምግብ ለማብሰል ወይም የህዝብ መጓጓዣ ለመጠቀም ይቸገራሉ። በህጻናት መንደር እንክብካቤ ውስጥያለፉ ወጣቶች በማሳደጊያ ተቋማት በእንክብካቤ ካለፉ ከአብዛኛዎቹ ወጣቶች ጋር ሲነጻጸሩ ትምህርት ላይ የተሻሉ ናቸው (ከአሥሩ ስምንቱ የ9ኛ ክፍል ፈተናን ያልፋሉ እንዲሁም 14 በመቶው በትምህርት ዲግሪ አላቸው)። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ የዕለት ተዕለት ተግባራትን ማስተዳደር ላይ ከፍተኛ ችግር አለባቸው። ከእንክብካቤ ከመውጣታቸው ረጅም ጊዜ አስቀድመው ቀላል እና ተጨባጭ የሆኑ ክህሎቶችን መማር ያስፈልጋቸዋል።

 

“የመጀመሪያ ሥራ እና የምኖርበት ቦታ ማግኘት እችላለሁ?”

  • የአፍሪካ ልማት ባንክ (እ.አ.አ. 2016) እንደገለጸው ከሆነ በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ወጣቶች ወደ ሥራ ፈላጊነት የሚመጡ ሲሆን በየዓመቱ የሚፈጠሩት ግን 3 ሚሊዮን አዳዲስ ሥራዎች ብቻ ናቸው። በወጣቶች ዘንድ ያለው ከፍተኛ የሥራ አጥነት መጠን በምስራቅ አፍሪካ በእንክብካቤ ውስጥ ላለፉ ወጣቶች ትልቅ ተግዳሮት ነው። በፈተና ጥሩ ውጤት ቢኖራቸውም እንኳን የዕለት ተዕለት ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን የሚያስችላቸውን ሥራ ለማግኘት ይቸገራሉ። በመንደሮች እና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባለባቸው አካባቢዎች ውስጥ ሥራ ለማግኘት ጠቃሚ በሆኑ ተጨባጭ በሆኑ የዕጅ ሞያዎች (ብየዳ፣ አናጢነት፣ የመኪና ጥገና፣ የመንገድ ላይ ንግድ የማሻሻጥ ክህሎቶች፣ ወዘተ) ዙሪያ የሞያ ትምህርት ማግኘትን የሚጠይቅ ሲሆን ይህንንም ሊማሩ የሚገባው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ ነው።  ከመንደሮች ወደ ከተሞች የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት ቤት ማግኘትን እና ኪራይ መክፈልን የሚያከብድ ሲሆን ይህም ተጨባጭ የሥራ ክህሎቶችን ይበልጥ አስፈላጊ የሚያደርግ ነው። በማህበረሰቡ ውስጥ አስፈላጊ እና ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎች ላይ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ ስልጠና ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።

    “በአዲሱ ማህበረሰቤ ውስጥ ካሉ ማህበራዊ ትስስሮች ጋር መገናኘት የምችለው እንዴት ነው?”

     

  • አሁን ያሉት የዝግጅት አሠራሮች ኖረውም እንኳን በማህበረሰብ ውስጥ ራስን ችሎ ወደመኖር የሚደረገው ሽግግር በጣም ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል በእንክብካቤ ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ይገልጻሉ። አብዛኛውን ጊዜ ለብቸኝነት እና ለጉዳት ተጋላጭ የመሆን ስሜት ይሰማቸዋል፣ በሚኖሩበት አዲስ ማህበረሰብ ውስጥ እንዴት ከሰው ጋር መግባባት እንደሚችሉ አያውቁም ወይም ከወላጆቻቸው ወይም የስጋ ዘመዶቻቸው  ጋር መልሰው ለመቀላቀል ይቸገራሉ። እንዲሁም በጎ ድጋፍ እና እገዛ የት ማግኘት እንደሚችሉ እና ከየትኞቹ አደገኛ ነገሮች መራቅ እንዳለባቸው (ማን ሊያታልላቸው ወይም ሊጎዳቸው እንደሚችል) አያውቁም። በማህበረሰቡ ውስጥ አዲስ ማህበራዊ ትስስሮችን ለመገንባት እገዛ ያስፈልጋቸዋል። ራሳቸውንም ከአደጋ እንዲጠብቁ   ምክር ያስፈልጋቸዋል።