ክፍለ ጊዜ 17/21

ገጽ 3/9 የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትን መረዳት እና ማክበር

የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትን መረዳት እና ማክበር

በርካታ ህጻናት ጎዳና ላይ ለመኖር የሚወስኑት ለምንድን ነው?
በጎዳና ላይ ለመኖር የሚወስኑ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጥናቶች ያሳያሉ። ከእነዚህ ህጻናት ውስጥ አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 16 ዓመት ነው። በምስራቅ አፍሪካ (እንዲሁም በዓለም ዙሪያ) ሰዎች የመኖሪያ ቀዬአቸውን ጥለው በመሄድ ተለቅ ያሉ ከተሞች ውስጥ መኖር ይጀምራሉ። በአዲስ ከተሞች ውስጥ ያሉ ከባቢ ሁኔታዎች በትላልቅ ቤተሰቦች ላይ እንዲሁም ለልጆቻቸው እንክብካቤ፣ ፍቅር እና ጥበቃ ለመስጠት ባላቸውን አቅም ላይ ጫና ያሳድራሉ። ድህነት እና ሥራ አጥነት (እንዲሁም ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ) በወላጆች ላይ ተጨማሪ ጫናን ይፈጥራሉ። ይህ በቤተሰቦች ላይ የሚፈጠር ጫና የቤት ውስጥ ጥቃት፣ ፍቺ፣ ሱሰኝነት፣ ትምህርትን ማቋረጥ እንዲሁም በልጅነት ማርገዝ እንዲጨምር ያደርጋል። በታንዛኒያ እና በኬንያ ውስጥ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች ውስጥ ወደ ግማሽ የሚጠጉት በዘመዶቻቸው እና/ወይም በሚያከብሯቸው ሰዎች ጥቃት የተፈጸመባቸው እንደሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከናወኑ ብሔራዊ ጥናቶች ያሳያሉ። በታንዛኒያ እና በኬንያ ከሚገኙ ሴት ልጆች ውስጥ አንድ ሦስተኛው የመጀመሪያ የወሲብ ተሞክሮአቸው ተገደው የፈጸሙት እንደነበር ገልጸዋል። ድህነት፣ የትዳር ግጭቶች እና በቤተሰቦች ውስጥ የሚፈጠሩ ጫናዎች በርካታ ህጻናት እና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆችን ከቤት እንዲጠፉ ያደርጋቸዋል። በሩዋንዳ ካሉት የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ውስጥ ከግማሽ በላዩ በህይወት ያሉ ወላጆች ያሏቸው ናቸው።
ምሳሌ፡- ብቻዋን ልጆቿን የምታሳድግ እናት ያላቸው በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ቁጥሩ እየጨመረ የመጣ አንድ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ምድብ ነው። በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች በቤተሰብ ዙሪያ ባለው ባህል መሠረት የሌለውን ወይም የሞተውን አባታቸውን በርካታ ሃላፊነቶች እና ግዴታዎች እንዲረከቡ እና ብቻዋን የምታሳድጋቸውን እናታቸውን እና ወንድም እህቶቻቸውን እንዲደግፉ ስለሚጠበቅባቸው አብዛኛውን ጊዜ ከቤት ይጠፋሉ። የጎዳና ተዳዳሪ ህጻን የነበረው ሙጋቦ “አራት ታናሽ እህቶች እና አምስት ወንድሞች ነበሩኝ። በጣም ድሀ ነበርን እንዲሁም የምትንከባከበን እናታችን ብቻ ነበረች። ቀኑን ሙሉ ቆሻሻ መልቀም መሥራት ነበረብኝ። ስትሞት አሥራ ሁለት ዓመቴ ነበር። ዘመዶቼም እናቴ ትታው የሄደችውን ንብረት በሙሉ እንደሚወስዱ እና በባህላችን መሰረት ታናሽ ወንድም እና እህቶቼን በሙሉ መደገፍ እንዳለብኝ ነገሩኝ። ይህን ማድረግ እንደማልችል አውቀው ነበር፤ ስለዚህ ልቤን ቢያደማውም ከቤት ጠፋሁ። አሁን አሥራ ሰባት ዓመቴ ነው፤ የምኖረውም ጎዳና ላይ ነው። በየቀኑ ስለ ታናሽ እህቶቼ እና ወንድሞቼ አስባለሁ” ብሏል።
ከጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ጋር የተያያዘ ሥራ መሥራትን ፈታኝ የሚያደርገው ምንድን ነው?

የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት አብዛኛውን ጊዜ በባለሥልጣን አካላት እና በማህበረሰቡ የሚታዩት እንደ ምስኪን ተጎጂዎች ወይም እንደ ወንጀለኛ ተደርገው ነው። እነዚህ ህጻናት አብዛኛውን ጊዜ የሚጠሩት ክብርን በሚነካ መጠሪያ ነው።

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መብት ስምምነት የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ከሁሉም ህጻን ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የሚከተሉት መብቶች እንዳሏቸው ይገልጻል፡- የጤና፣ የሥነ-ምግብ እና የትምህርት አገልግሎት የማግኘት። ሆኖም ግን እነዚህ መብቶች ለአብዛኛዎቹ ህጻናት ከእውነታው የራቁ ናቸው እንዲሁም በየቀኑ በህይወት ለመኖር መታገል ይኖርባቸዋል። እንዲያውም እነዚህ ህጻናት የልጅነት ጊዜያቸው ከማብቃቱ ረጅም ጊዜ አስቀድመው ያለወላጆቻቸው ህይወትን ለመቋቋም የሚያስችል ማስተዋል፣ የፈጠራ ችሎታ እና መንፈስ ስላላቸው ሊደነቁ ይገባል። በየቀኑ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ፈተናዎችን የሚወጡ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡- ወላጆቻቸውን ማጣት፣ ረሀብ፣ መድልዎ እንዲሁም በጎዳና ላይ ከመኖር ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎች በሙሉ። አንዳንዶቹ በህይወት ለመኖር ሲሉ ወንጀለኞች የሚሆኑ ቢሆንም እንደዚያም ሆኖ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል።

መልሶ ማገገም እና በአደራ ቤተሰብ ውስጥ መኖር ፈታኝ ሊሆን ይችላል ምክንያቱም እንዲህ ያለው ህጻን በአዋቂዎች ላይ ምንም እምነት የለውም እንዲሁም በጣም የሚቀራረበው በጎዳና ላይ ከሚያውቃቸው ሰዎች ጋር ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ህጻን “እናቴም አባቴም ጎዳና ነው” ብሏል። እርዳታ ለማድረግ የሚደረጉ በርካታ ጥረቶች የማይሳኩትም ከእምነት ማጣት የተነሳ ነው፤ እንዲሁም ህጻናት አብዛኛውን ጊዜ ከአደራ ቤተሰብ ወይም ከማገገሚያ ማዕከል ይጠፋሉ። ከተረዳናቸው እና ካከበርናቸው ግን በእንክብካቤ ሰጪዎቻቸው ላይ ያላቸውን እምነት ደረጃ በደረጃ ልንገነባው እንችላለን።

የቡድን ውይይት

10 ደቂቃ

  • በማህበረሰባችን ውስጥ በባለስልጣን አካላት እና በህዝቡ አመለካከት ውስጥ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት የሚታዩት እንዴት ነው?
  • ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ውስጥ ቢሆኑም እና ፍቅር እና እንክብካቤ ባያገኙም እንኳን ያንን አልፈው የኖሩ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ምሳሌዎችን እናውቃለን?
  • በአዋቂዎች ላይ ያላቸውን ዕምነት ለማደስ በምንሞክርበት ወቅት ህጻናቱ የሚሰጡን ምላሽ ምን ይመስላል?